Minister's Message Minister's Message

የቴክኖሎጂ እድገት እየተፋጠነ በሚገኝበት ዓለም ውሰጥ የምንገኝ በመሆኑ የኢኖቬሽናዊ ቴክኖሎጂ የእድገት ሂደትን መለስ ብለን ብንቃኝ ብዙ  አስደማሚ ነገሮችን እንደምንመለከት ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ ባሻር የሰው ልጅ ህልውናና የሀገር እድገትም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ውጭ ማሰብ የማይቻልበት ደረጃም ላይ ተደርሷል፡፡ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና  የኢኖቬሽናል ቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በዚህ ተለዋዋጭ የቴክኖሎጂ ዓለም በተወዳዳሪነት መዝለቅ የሚቻለው ራስን ከእውነታው ጋር አስማምቶ ተዘጋጅቶ መስራት ሲቻል ነው፡፡  ለዚህም ነው ሀገራት የቴክኖሎጂና  ኢኖቬሽን ፖሊሲዎቻቸውንና ተግባሮቻቸውን ከራሳቸው ነባራዊ  ሁኔታ ጋር አጣጥመው ለመፈጸም ያላሰለሰ ጥረት በየጊዜው የሚያደርጉት፡፡  ይህ እውነታም በሀገራችን በተተገበረው እና በመተግበር ላይ ባለው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፖሊሲና ስትራቴጂ አፈጻፀም ሂደት የታየ  ነው፡፡
ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ውጤት ለማምጣት በተነደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች  የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ በመፈጸም መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት  እንዲቻል ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ በግልጽ እንደተቀመጠው ለሀገሪቱ ማህበራዊና  ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ የህዝቡን ኑሮ በማሻሻል ድህነትን ማስወገድ እንዲቻል የዘርፉን ተዋናዮች ለማብቃት እየተሞከረ ቆይቷል፡፡
በቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት፣ በሰው ሃይል ልማት፣ በማምረቻና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በምርምር፣ በጥራት መሰረተ ልማት፣ በአዕምሮአዊ ንብረት ስርዓት፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትና ኢንዱስትሪ ትስስር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ፣ በአካባቢ ልማትና ጥበቃ እንድሁም ዓለም አቀፍ ትብብር ቴክኖሎጂያዊ አቅምን እና ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የተደረጉት ጥረቶች አመላካች ናቸው፡፡
በእነዚህ ዘርፎችና ተቋማት ሃገራችን ለያዘቸው የመልማት ውጥንና የትራንስፎርሜሽን ጉዞ  የሚውል ቴክኖሎጂ ከኢንዱስትሪው ፍላጎት በመነሳት በማፈላለግ፣ በማቅረብ፣ በመቅዳትና በማላመድ ብቃቱ የተረጋገጠ የሰው ሃይል እና ተላማጅ ቴክኖሎጂን በመገንባት፣ የማቀብ እና የማሸጋገር ተግባርን እየተወጣን እንገኛለን፡፡ እነዚህንና መሰል ተግባራት በኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ስርዓት በመታገዝ አጠናክረን ለመቀጠል በትኩረት መስራት የሚጠበቅብን ወቅት ላይ መሆናችንን እንገነዘባለን፡፡ 
የኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ኢኖቬሽን ስርዓቱን በመምራት  ሂደት ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል በአዋጅ ቁጥር 1097/11 እንደገና ተቋቁሞ ጥልቀት ያላቸው ኃላፊነቶችና ተግባራት ተሰጥተውት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይህም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍን በማጠናከርና ወጥነት ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ በማስፈጸም ለኢኮኖሚ ልማት ያለውን ሚና በተገቢ ሁኔታ እንዲወጣ አዲስ አቅምን ይፈጥርለታል፡፡
ይህንም ማሳካት እንድንችል  የኢኖቬሽናል ቴክኖሎጂና የምርምር ስራዎች በጠራ አመለካከት እና የስራ ባህል እንዲመሩ በቂ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶችና የፈጠራ ሃሳብ ያለቸውን አካላትም መደገፍ  ስለሚገባ ይህኑ ጥረት እውን የምናደርግበትን አቅም በመፍጠር ላይ እንገኛለን፡፡  የምናደርገው ድጋፍ ያልተቆራረጠ ወቅቱን የጠበቀ እና ዘላቂነት ያለው እንዲሆን ኢኖቬተሮች፣ ቴክኖሎጂስቶችና ተመራማሪዎች ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገትና ህዳሴ ጉዞ የሚኖራቸውን ድርሻ የሚያጎላና የሚሳይ በሆነ መልኩ እንዲሆን ጥረታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል፡፡ 
በመሆኑም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂና ምርምር አቅም ግንባታ ሂደት በቅድመ ዝግጅትና ትግበራ ደረጃዎች ከባለድርሻ አካላትና ከሚመለከታቸው የመንግስት መ/ቤቶችና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በየደረጃቸው የሚተገበረውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ የማሻሻል ስራን ሰርተናል፡፡  ይህን ፖሊሲ በመተግበር  እንደ ሀገር ወጥ የሆነ እና ውጤታማ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ኢኖቬሽን ስርዓት የመዘርጋት ሂደቱም በመረጃ ተደራሽነት  መደገፍ ስላለበት የተቋማችንን አጠቃላይ ገጽታ እና የየእለት እንቅስቃሴ ማሳየት እንዲቻል ይህን ዌብ ሳይት በተደራጀ መልኩ አዘጋጅተናል፡፡    ከዌብሳይታችን አስፈላጊ መረጃዎችን በመጠቀም፣ በማዳበር፣ ብሎም ግብረ መልስ በመስጠት ለስራችን ስኬት የበኩላችሁን እንድትወጡ መልዕክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡
ጌታሁን መኩሪያ(ዶ.ር ኢንጅ)