“የአንድ ዓመት ጉዞ፡- ዲጂታል ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ” በሚል “የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ 2025” ፀድቆ ወደ ስራ ከገባበት ጀምሮ የተሰሩ ስራዎችና በቀጣይ ሊሰሩ በሚገባቸው ስራዎች ዙሪያ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ መክረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ፒ ኤች ዲ) ባለፈው አንድ አመት ምቹ የኢኖቬሽን ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር፣ የዲጂታል ስትራቴጂ 2025 ምንነትን ማሳወቅና ተቋማት በእቅዳቸው ውስጥ እንዲያካትቱት የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን በማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተቋማት በትብብር እንዲሰሩ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
በዝግጅቱ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ የኢኖቬሽን ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ በርካታ ስራዎች ስለመሰራታቸው ተብራርቷል።
የዲጂታል ክፍያ፣ የትራንዛክሽን አዋጅ፣ የስታርት አፕ አዋጅ፣ የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ በማርቀቅና በማፅደቅ በዲጂታል ዘርፍ አዲስ ከባቢያዊ ሁኔታ መፈጠሩ ተብራርቷል።

በዝግጅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩትና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊዎች የዘርፉ ስራዎችን የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።