ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስራ ፈጠራ የምትመች ሀገር ለመፍጠር መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ደርጅቶች ( tech startups) እና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን በቀላሉ ወደ ገበያ እንዲያስገቡ የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡

አይስ አዲስ (Iceaddis) የተሰኘውና ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚሰራው ድርጅት 10ኛ አመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው፡፡

የአይስ አዲስ መስራችና ስራ አስኪያች አቶ ማርቆስ ለማ ድርጅቱ ለ163 የስራ ፈጣሪዎችና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ምቹ ሃሳበቸውን እንዲያበለፅጉና ወደ ገበያ እንዲገቡ እንዲገቡ የመሰረት ድንጋይ መጣል መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ( tech startups)፣ ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች፣ ለቴክኖሎጂ አልሚዎች የመስሪያ ቦታ በማመቻቸትና ስልጠና በመስጠት ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ምቹ ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠር እንሰራለን ብለዋል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚነስትር ዴኤታ አህመዲን መሃመድ (ፒ ኤች ዲ) አይስ አዲስ የመንግስት ቢሮክራሲ ለቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪዎች ምቹ ባልሆነበት ወቅት ተመስርቶ ለዚህ ውጤት በመብቃቱ አድንቀዋል፡፡

ይህንን ችግር በመረዳት መንግስት ለዘርፉ ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻው ውስጥ የተካተቱ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያ ስራን ጨምሮ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ፀድቆ ወደ ስራ መግባት፣ የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች አዋጅ መዘጋጀት፣ የኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ ዝውውር አዋጅ መፅደቅ፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የዲጂታል ክፍያ ስርዓትና ኢኮሜርስ ላይ በተልዩ ትኩረት እየተሰራ ስልመሆኑ አብራርዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ፒ ኤች ዲ) በአንድ ተቆጣጣሪ ብቻ ተይዞ የነበረውን የቴሌኮም ዘርፍ ወደ ግል የማዛወር ሂደት ውድድርን በመፍጠር ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ምቹ ከባቢ ሁኔታን ፈጣሪ የሆነው አይስ አዲስ 10ኛ አመት በዓሉ ላይ በዘርፉ ያሉ ችግሮችና የወደፊት ምቹ ሁኔታዎች ላይ የተመለከቱ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook