የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ያለውን የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ዝግጁነት የዳሰሳ ጥናት አቅርቧል።
በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ ሃዋሳና አዳማ ከተሞች እንዲሁም በየከተሞቹ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉበትን ደረጃ አጥንቶ ክፍተቶችን ለይቷል።
በዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ መሰረተ ልማትና የሰው ሃይል መኖሩን ቡድኑ ያረጋገጠ ሲሆን የአይሲቲ ዲፓርትመንት የሌላቸው የከተማ አስተዳደሮች መኖራቸውንም ተመልክቷል።

የመድረኩ ተሳታፎዎች
በአዲስ አበባ የተሻለ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ጅማሮዎች ሲኖሩ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በተናጠል ጅምር ስራዎች መኖራቸው ተገምግሟል።
ሁለት ክልሎችን እያስተናገደ ያለው የሀዋሳ ከተማ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሰራቸውን ስርዓቶች በከተማዋ ለመተግበር እየሰራ መሆኑን ገምግሟል።
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተነሳሽነትና በቢሮ ደረጃ የተጀመሩ ስራዎች ሲኖሩ እነዚህን ወደ ከተማ ማስፋት ይጠይቃል ተብሏል።
ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ችግር አለበት የተባለው የአዳማ ከተማ አስተዳደር የነዋሪነት መታወቂያ ዲጂታል ማድረግና የጋብቻ ቅፅን ኦንላይን መስጠት የመሳሰሉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
በሁሉም ከተሞች የመሰረተ ልማት ችግርና የአቅም ግንባታ ክፍተቶች መኖራቸው ተለይቷል።
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተሸል መሰረተ ልማት ሲኖራቸው ሲስተሞችን በማልማት ወደ ገበያ ጭምር ያወጡ መኖራቸው ተገልፁዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በመሰረተ ልማትና በሰው ሃይል የተሻለ አቅም ስላላቸው አቅማቸውን አሟጥጦ መጠቀም እንደሚገባ ተጠቁሟል። ቡድኑ በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛ ጊዜና በረጅም ጊዜ ሊተገበሩ የሚችሉ ምክረ ሃሳቦችንም አቅርቧል።