መንግስት ጠንካራ የበይነ መረብ ግንኙነት (ኢንተርኔት) ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን፣ ኢንተርኔት ሶሳይቲ፣ አይሲቲ-ኢቲ ከፕሪዳ (የፖሊስና ቁጥጥር ኢኒሺየቲቭ ለዲጂታል አፍሪካ) ከተሰኘውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የበይነ መረብ አስተዳደር ስልጠና ተጠናቅቋል፡፡

የስልጠናው ዓላማ በዘርፉ ላሉና ከመንግስት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም ተማሪዎችና ከዘርፉ ማኅበረሰብ ለተውጣጡ የተለያዩ ሰዎች በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አስተዳደር ዙሪያ አቅማቸውን መገንባት ነው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል አቢዮት ባዩ (ፒ ኤች ዲ) በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ሚና በሚጫወተው ጠንካራ የበይነ መረብ ግንኙነት ለዜጎች ማዳረስ ላይ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንተርኔት ተደራሽነት ቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ ፍላጎት ነው ያሉት ጀነራል ዳይሬክተሩ በዘረፉ ተወዳዳሪ ተቋማት እንዲኖሩ ለማድረግና ዜጎች አማራጭ የበይነ መረብ ግንኙነት እንዲኖራቸው መንግስት ዘርፉን ለግል ተቋማት ክፍት ማድረግ መጀመሩን አብራርተዋል።

በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆንም የወጣቶች የዲጂታል ክህሎት ማሳደግ ላይ ይሰራል ነው ያሉት።

ስልጠናው የበይነ መረብ ግንኙነትን ማሳደግና መጠቀም እንዲሁም የኢንተርኔት አስተዳደር ላይ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ የተዘጋጀ ነው።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook