ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የለማ “የተቀናጀ የጭነት ትራንስፖርት ማስተዳደሪያ ስርዓት” ተመረቀ።

ስርዓቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋሙ በነበረው የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት አማካኝነት የለማ ነው።

በዘርፉ ፍቃድ ለማውጣትና ለማደስ፣ አዲስ ተሽከርካሪ ለማስመዝገብ፣ የድንበር ተሻጋሪ መታወቂያ ለማውጣትና ለማደስ፣ ክፍያ ለመፈፀም፣ ስምሪት ለመቆጣጠር፣ የጭነት አይነትና የጉዞ ርቀትን ለመለካት ስርዓቱ ያስችላል።

የትራንስፖርትና ሎጂስትክ ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የተቀናጀ የጭነት ትራንስፖርት ማስተዳደሪያ ስርዓቱ በደረቅና ፍሳሽ ማመላለሻ ትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀይር ነው ብለዋል።

የትራንስፖርት ዘርፉ ዘመናዊ፣ ብቁና ቀልጣፋ እንዲሆን እየሰራን ነው ያሉት ሚኒስትሯ ስርዓቱ ቀልጣፋና ዘመናዊ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ኦፕሬተሮችን ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) የኤሌክትሮኒክ ኮመርስን በኢትዮጵያ በተሟላ ደረጃ ለመተግበር ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ዘመናዊ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ችግሮች በአሰራር፣ በብቁ የሰው ሃይል፣ በአደረጃጀትና በቴክኖሎጂ መቅረፍ ከተቻለ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሎጂስቲክስ ሃብ ማድረግ ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የተቀናጀ የጭነት ትራንስፖርት ማስተዳደሪያ ስርዓቱ የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት የሆነውን የትራንስፖርት ዘርፍ ለማዘመን ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ስርዓቱ የዘርፉ ኦፕሬተሮች አገልግሎት ለማግኘት ወደ መስሪያ ቤት በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው ባሉበት አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው ሲሆን ክፍያን ለመፈፀም ደግሞ ከቴሌ ብር ጋር እንዲተሳሰር ተደርጓል።

በቀጣይ ከሁሉም ባንኮች ጋር ለማስተሳሰር ይሰራል። ከነገ ጀምሮ የጭነት ተሽከርካሪዎች ፍቃድ ለማውጣትና ለማደስ በድረ ገፅ አድራሻ ITMS – Home (motr.gov.et) መስተናገድ ይችላሉም ተብሏል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook