ሰሞኑን የተመረቀው “ብሄራዊ የህብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃ ማዕከል የዲጂታል አሰራር” ምን አዲስ ነገር አለው?

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት እና ማስተር ካርድ በጋራ በመተባበር የጤና ድንገተኛ መረጃ የጥሪ ማዕከልን አቋቁመው የዲጂታል አሰራር ታክሎበት ተመርቋል። የመረጃ ማዕከሉ አዲሱን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ጨምሮ የኮቪድ 19፣ የጊኒወርም፣ የቢጫ ወባና የኮሌራ በሽታዎችን በሚመለከት ዜጎች በነፃ የስልክ መስመር እየደወሉ መረጃ የሚያገኙበት ስርዓት ነው። በ5 ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ፣ አፋርኛ እና ሶማልኛ) አገልግሎት ይሰጣል። በማንኛውም ጊዜ ተጨማሪ ቋንቋዎችንም ማካተት ይቻላል።

ይህ አውቶሜትድ የተደረገ ስርዓት በጤናው ዘርፍ ያሉ የመረጃ አያያዞችን የሚያዘምንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በአንድ ጊዜ መስተናገድ የሚችሉበት ነው። ከዚህ ቀደም በነበሩ አሰራሮች መረጃ ፈላጊ ዜጋ መረጃውን ወደሚሰጠው የጥሪ ማዕከል ሲደውል መስተናገድ የሚችለው በተመደቡት የባለሙያዎች ቁጥር ልክ ብቻ ነበር። ለምሳሌ አንድ የጥሪ ማዕከል ውስጥ የተመደቡ ሰራተኞች 10 ቢሆኑ በአንድ ጊዜ ጥሪ ማስተናገድ የሚችሉት 10 ሰዎችን ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ ያሉ ሰዎች ወይ ወረፋ እስኪደርሳቸው ለመጠበቅ ይገደዳሉ ወይንም ወረፋ ላይደርሳቸውም ይችላል።

በዚህኛው ስርዓት ውስጥ ግን የሚሰጡ መረጃዎች ተቀድተው የተቀመጡ በመሆናቸው ለደዋዩ በቀጥታ እንዲደርሱት ይደረጋል። ደንበኛው የማዕከሉን ሰራተኞች ግዴታ ማግኘት ሲፈልግ ብቻ ነው ጥሪው ወደ ሰራተኞቹ የሚተላለፈው። ከዚያ ውጭ ያሉ ደዋዮች በሙሉ በቅጂ መላሽ በሆነው ስርዓት ይስተናገዳሉ።በጥሪ ማዕከሉ በአንድ ጊዜ 120 ጥሪዎች መስተናገድ የሚችሉ ሲሆን በ24 ሰዓት ውስጥ 60ሺ ጥሪዎችን ማስተናገድ ይቻላል።

ኮቪድ ምን አስተማረ?

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ስራዎች በዲጂታል መልኩ እንዲሰሩ በብዙ መልኩ አስገድዷል። በተለምዶው የሚሰሩ የነበሩ አሰራሮች በሙሉ ከአካላዊ ንክኪ ውጭ እንዲሆኑ መደረጉ ለዲጂታል አሰራሮች በር ከፍቷል፡፡ በሽታውን የሚመለከቱ መረጃዎች ዜጎች በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ በ951 ነፃ የስልክ መስመር ላይ መረጃ ሲሰጥ ነበር፡፡ ይህ አሰራር ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ የማስተናገድ ክፍተት ቢኖርበትም እንደ መረጃ ምንጭ ሲያገለግል ቆይቷል።

ይህ ማዕከል ለሁለት አመት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነው። በዚህ ሁለት አመት ውስጥ ደውለው መረጃ ያገኙ ሰዎች ቁጥር ወደ 3ሚሊየን የሚጠጉ ናቸው። በአዲሱ የዲጂታል አሰራር ግን በሁለት ወር ውስጥ በቂ ማስታወቂያ ሳይሰራ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ደንበኞች ተስተናግደዋል። በዚህ መሰረት ኮቪድ የዲጂታል አሰራሮችን ለመማርና ለመተግበር ረድቶቷል።

አዲሱ 8335 የድንገተኛ በሽታዎች መረጃ የጥሪ ማዕከል ምን አዲስ ነገር አለው?

የጥሪ ማዕከሉ አምስት ዓይነት የበሽታ አይነቶችን መረጃ የሚሰጥ ሲሆን በኦቶሜሽን ስራ (በማሽን ምላሽ) የተዘጋጀ ነው። ደንበኛው ቀጥታ ሲደውል የሚፈለገውን መረጃ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ምላሽ ያገኛል። በርካታ ሰዎች በአንድ ጊዜ እንዲስተናገዱ ያደረጋል።

ደዋዩ የጥሪ ማዕከሉ ውስጥ ያሉ ሰራተኞችን ማግኘት ቢፈልግ እና ሁሉም ሰራተኞች ስልክ ይዘው መመለስ ባይችሉ ጥያቄውን በድምፅ ቀርፆ ማስቀመጥ ይችላል። የጥሪ ማዕከሉ ሰራተኞች ለጥያቄው ምላሽ ለደንበኛው ደውለው መስጠት ይችላሉ። ወይንም ደግሞ ቀን ላይ በርካታ ደንበኞች ስለሚደውሉ እና የጥሪ ማዕከሉ ባለሙያዎች ስራ ሊበዛባቸው ስለሚችል ሌሊት የሚገቡ ተረኛ ባለሙያዎች ከደንበኞች የተላኩ በድምፅ የተቀዱ ጥያቄዎችን መመለስ ይጀምራሉ። ባለሙዎቹ በድምፅ የቀረፁትን ምላሽ ወደ ሲሰተሙ ያስቀምጡትና ሲሰተሙ ሌሊት ደንበኛው ሊተኛ ስለሚችል ሲነጋ በራሱ አሰራር መሰረት ለደንበኛው ደውሎ የተቀረፀውን ምላሽ ያስማዋል።

አውቶሜሽን (የማሽን ምላሽ) ምን ጠቀመ?

በቴክኖሎጂው ዓለም ውስጥ ኦቶሜሽን ተደጋጋሚ ስራዎችን ማሽን አስቦ እንዲመልስ በማድረግ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። በዚህ የጥሪ ማዕከል ውስጥም ደንበኞች በተደጋጋሚ የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎችን ማሽን እንዲመልስ በማድረግ ባለሙዎች ወደ ሌሎች አንገብጋቢ ስራዎች እንዲመለሱ አስችሏል። ለምሳሌ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውስጥ በርካታ ሰዎች በየቀኑ በበሸታው የተያዙ፣ የሞቱና ያገገሙ ሰዎችን መረጃ ማወቅ ይፈልጋሉ። ይህንን መረጃ ለደንበኛው ባለሙያው ከሚሰጠው ይልቅ የየቀኑን ሪፖርት ማሽን እንዲነግረው ማድረግ ተችሏል።

ቴክኖሎጂው የት ለማ?

የቴክኖሎጂ እድገት የሚመጣው ቴክኖሎጂ በመጠቀም ብቻ አይደለም። በመቅዳትና በማልማት ነው። ይህ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ በኢትየጵያዊያን የለማ እና ቁጥጥር የሚደረግበት ነው። መረጃዎቹ የሚቀመጡትም በኢትዮጵያ ተቋማት ውስጥ ነው። ይህ መሆኑ አዳዲስ አሰራሮችን ለመጨመር፣ ወደ ሌሎች ዘርፎች ለማሸጋገር፣ ለማዘመን እና ከስርዓቱ ጋር ቤተሰብ ለመሆን የራሱ አስተዋፅኦ አለው። ይህ በመሆኑ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በዓለም ላይ ሲከሰት ገና ወደ ኢትዮጵያ ሳይገባ ስለ በሽታው ምንነት ዜጎች መረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል። አሁን በ 8335 ላይ ማንኛውም ሰው ስለ ዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ መረጃ ማግኘት ይችላል። ስርዓቱ በሀገር ውስጥ መልማቱ አዳዲስ ሃሳቦችንና አሰራሮችን በፍጥነት ለመጨመር እድል ሰጥቷል። ሌላው በሀገር ውስጥ መልማቱ ደግሞ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ ከምናመጣቸው ቴክኖሎጂዎች ወጪ ታድጎናል።

የመረጃ ክምችቱ ለምን ይጠቅማል?

እንደ ሀገር የተደራጀ እና ዲጂታይዝ የተደረገ የመረጃ እጥረት አለ። ይህ መረጃ ባለመኖሩ መረጃን ተንትኖ መጪውን ለመተንበይ አልተቻለም። ለምሳሌ በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የበርካታ አመታት መረጃዎች አሉት። ነገር ግን እነዚህ መረጃዎች በዲጂታል መልክ ባለመቀመጣቸው ተንትኖ ቀጣይ ጊዜያትን ለመተንበይ አስቸጋሪ ያደርገዋል። በዚህኛው የመረጃ ጥሪ ማዕከል መረጃዎች በሙሉ ዲጂታይዝ በሆነ መልኩ ይገኛሉ። ደንበኞች የሚያተኩሩባቸው ጥቄዎች፣ የትኛው ደንበኛ ከየትኛው አካባቢ ምን አይነት መረጃ እንደሚፈልግ፣ የትኛው አካባቢ አዲስ በሽታ እንደተከሰተ፣ የትኛው አካባቢ የትኛው መረጃ ተፈላጊ እንደሆነ፣ በምን ምክንያት እና የመሳሰሉትን መረጃዎች በማጥናትና በመተንተን እንደ ግብኣት ለመውሰድ ይቻላል። ይህ የመረጃ ጥርቅም ደግሞ ለትልቅ ዳታ ትንተና ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል። በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠትም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook