ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ መደበኛ ስራውን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራምንም እንደሚደግፍ ይፋ አድርጓል።

በድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ የተመራው የአመራር ልዑክ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጋር መክሯል።

በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ የተሰጠው ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ መደበኛ ስራውን እያከናወነ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አንዋር ሱሳ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ሚዲያው በኢትዮጵያ ላይ ባደረገው ዘመቻ ምክንያት የፀጥታ ስጋት የገባቸው አንዳንድ ሰራተኞቹ ከኢትዮጵያ መውጣታቸው እንዳሳዘናቸው የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው መደበኛ ስራቸውን እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ የተደረገውን የውሸት ዘመቻና መሬት ላይ ያለውን እውነት ከሳፋሪኮም በላይ ምስክር ሊሆን የሚችል የለም ብለዋል።

ከሚዲያ ዘመቻ ውዥንብር ራሳቸውን በማላቀቅ ስራቸውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሰሩ ያሳሰቡት ሚኒስትር ዴኤታዋ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አረጋግጠዋል።

መሬት ላይ ያለውን የኢትዮጵያን እውነትም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያስረዱ ጠይቀዋል።

ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በገባው የረጅም ጊዜ የንግድ ስምምነት መሰረት ድርጅቱ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ለመደገፍም እንደሚሰራም ቃል ገብቷል።

ድርጅቱ ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆኑ እቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ ሲሆን ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሰራተኞችም በቅርቡ ወደ ስራ ይመለሳሉ ተብሏል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook