በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር ለመስራት እና የስፔስ ቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ እና በተግባራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች የማማከርና የመደገፍ ዓላማ ያለው ስምምነት ተፈረመ።

የስምምነት ሰነዱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር በለጠ ሞላ (ፒኤችዲ) እና የ ORION AST ኩባንያ ባለቤትና ፕሬዚዳንት ሚስተር አሌክሳንደር አልቪን ፈርመውታል።

በፊርማ ስነስርዓቱ ክቡር ሚኒስቴር ዶክተር በለጠ ሞላ እንዳሉት ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ሁኔታ፣ የአፍሪካ ሕብረትን የልማት ስትራቴጂዎች፣ የሕብረቱን የ2063 አጀንዳ እና በ2030 ዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) ላይ የተመሰረተ የአስር ዓመት አገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ አውጥታ በመተግበር ላይ ትገኛለች።

አገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት እቅዱ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፎች እንዲታገዝ በማሰብ የኢትዮጵያ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ የአፍሪካን የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስትራቴጂ 2024 (STISA-2024) የህብረቱን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን አቅጣጫዎችን የተከተለና ዘርፉ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ሚናዎችን ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

STISA-2024 እንደ ግብርና፣ ኢነርጂ፣ አካባቢ፣ ጤና፣ የመሰረተ ልማት፣ ማዕድን፣ የአካባቢ ደህንነት ና ውሃ የመሳሰሉ ወሳኝ ዘርፎችን ተጠብቀው በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ለአዳዲስ አሰራሮችና ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው መከናወን ያለባቸውን ጉዳዮች ያስቀመጠ ነው ብለዋል።

አሕጉራዊና አገራዊ የዘርፉ ስትራቴጂዎች ስኬት የአጋር አካላት ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መስኮች ለማጠናከር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

የሕዋ ቴክኖሎጂ ዘርፍን ለድህነት ቅነሳ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለበሽታ መከላከልና ቁጥጥር፣ ለመረጃ ልውውጥ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ እና የሀብት ፈጠራ ስራዎችን ለማገዝ ጥቅም የሚሰጥ ነው።

በዚህ ረገድ እንደ ORIIN AST አስት አይነት ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለመስራት ያሳዩትን መነሳሳት አድንቀዋል።የ ORIIN AST ኩባንያ ባለቤትና ፕሬዚዳንት ሚስተር አሌክሳንደር አልቪን በበኩላቸው ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር በተተግባሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎችና በሕዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ በትብብር ለመስራት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

ስለ ድርጅታቸው አጠቃላይ ምልከታ ያቀረቡት ሚስተር አልቪን በሚኒስቴር መ/ቤቱ የተሰጣቸውን አፋጣኝ ምላሽ አመስግነው በቀጣይ በትብብር መስኮቹ በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባት ያስችለናል ብለዋል።

የስምምነቱ ዓላማ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር ለመስራት በተለይም የሕዋውን ሴክተር ለማሳደግ እና በተግባራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር መስኮች የማማከርና የመደገፍ ስራ በመስራት ዘርፉ ለአገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ማገዝ ነው።

ስምምነቱ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ፣ የሁለትዮሽ አሰራሮችን የሚያግዝ፣ የሀብት አጠቃቀምንና የባለቤትነት ስሜትን የሚጨምር፣ ቀጣይነት ያለው የስራ አመራር ለመዘርጋት የሚያስችል፣ በትብብር መስራት በተፋራራሚ አካላት መካከል እንዲኖር አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሚፈጸም ይኾናል። ስምምነቱንም ለማሳካት ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት ተለይተው ተቀምጠዋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook