በቴክኖሎጂ የሰው ሀብት ልማት እና አቅም ግንባታ ላይ መስራት ከፍተኛ የስራ ፈጠራ ክህሎት ያላቸው ዜጎችን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተገለፀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከUNDP እና ከኢንተርፕርነር ሺፕ ልማት ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን በኢኖቬሽን ስነ ምህዳርና ስራ ፈጣራ ዙሪያ በዘርፉ ላሉት ከሚኒስቴር መስሪያቤቱና ከክልሎች የተውጣጡ ሀላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናው በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ የፈጠራ ስርዓት ምህዳር ነባራዊ ምንነት፣በጀማሪ የቴክኖሎጂ ስራ ፈጣራዎች አካታች ፕሮግራም ትግበራ እና አመራር፣በዘርፉ ያሉ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ፣ የኢንተርፕርነርሺፕ እና የፈጠራ ፕሮግራሞች፣ የእሴት ፈጠራ ልምምድ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ በይሳ በዳዳ (ፒ ኤች ዲ) የቴክኖሎጂ ክምችት እና የፈጠራን ሀሳብ የሚያበረታታ ስርዓት በመዘርጋት ሀገራችን ያላት እምቅ ሀብት በቴክኖሎጂ በመደገፍ ወደ ሀብትና ልማት መቀየር የሚችል የሰው ሀይል በማፍራት ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ልማት ዋናው ምንጭ የሳይንሳዊ እና የቴክኖሎጂ እድገት መሰረታዊ መርሆችንና አቅጣጫዎችን የሚወስኑ ሰዎችንና አምራች ሀይሎችን በማልማት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በሀገራችን የሚገኙት የተፈጥሮ ሀብቶች በቴክኖሎጂ በመደገፍ ያለውን የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት እንደሚሰራም አብራርተዋል።