በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኮንፈረንስ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም የሚወክል በመሆኑ ለስኬታማነቱ በትኩረት እየሰራን ነው:- ዶ/ር አህመዲን መሐመድ

የአለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ጉባኤ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ኮሜቴ ዝግጅቱን የተመለከተ ስብባውን አካሂዷል።

በአፍሪካ ለመጀሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ኮሚቴው አንስቷል።

የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኮንፈረንስ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም የሚወክል በመሆኑ ለስኬቱ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኮንፈረንስ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከዓለም ሀገራት ልምድ የምንለዋወጥበትና የኢትዮጵያን ገፅታ የምንገነባበት ይሆናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለዝግጅቱ በስኬት መጠናቀቅ የሚመለከታቸው ሁሉ በትብብር እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የብሄራዊ ኮሚቴው ፀሃፊ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂ.) ጉባኤው የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት የወደፊት አቅጣጫዎች የሚነደፍበት በመሆኑ ኢትዮጵያ ለዘርፉ ማሻሻያዎች የሚሆኑ ልምዶችን ትቀስምበታልች ብለዋል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ ተቋማት የተዋቀረው የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ልማት ጉባኤ አዘጋጅ ሀገር ብሄራዊ ኮሚቴ ዝግጅቱን በበላይነት የሚመራ ሲሆን ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 11 ኮሚቴዎችንም ያስተባብራል።

የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ልማት ጉባኤ በየ4 ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን 8ኛው ጉባኤ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከግንቦት 27/2014 ጀምሮ ይካሄዳል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook