የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና “ስቴም ፓወር” (STEMpower) ለቡራዩ ልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ቤት ግንባታ የቤተ-ሙከራ እቃዎችን ለማሟላት የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል፡፡
ሰምምነቱ የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ቤትን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በሂሳብ እና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ የመማሪያ ቁሳቁሶችን ለማሟላት እና አነዚህን የቤተ ሙከራ እቃዎችን የሚገጥም የባለሙያ እቅርቦትን ያካተተ ነው፡፡የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒ ኤች ዲ) ለሁሉም ልዩ ችሎታ ያላቸው ኢትዮጵያውያን መፍለቂያ ታስቦ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከግንባታው መጠናቀቅ ጎን ለጎን የቤተ ሙከራ መሳሪያዎችን የማሟላት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ስቴም ፓወር እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የስቴም ፓወር የኢትዮጵያ ተወካይ ስሜነው ቀስቅስ (ፒ ኤች ዲ) ለቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ ትምህርት ቤት የቤተ ሙከራ መሳሪያዎችን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የቤተ ሙከራ እቃዎችን ብቻ ሳይሆን መሳሪያዎቹን የሚገጠም የባለሞያ ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒ ኤች ዲ) እና የስቴም ፓወር የኢትዮጵያ ተወካይ ስሜነው ቀስቅስ (ፒ ኤች ዲ) ፈርመውታል፡፡”STEMpower” ሁለት የቤተ-ሙከራ ክፍሎችን ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን የማደራጀት ስራ ለመስራት ነው ከስምምነት የተደረሰው፡፡