በኢትዮጵያ የሞባይልና በይነመረብ ተጠቃሚዎች እና የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነት እየጨመረ ነው።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችላትን የተለያዩ መደላድሎችን እየፈጠረች ትገኛለች፡፡ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ቅንጅታዊ አሰራር በትልቁ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት ከንግዱ ማህበረስብ፣ ተቋማት ከተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ ከተቋማት እንዲሁም ከአገልግሎት ፈላጊው ማህበረሰብ ጋር መቀናጀት ይኖርባቸዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አሳሪ የሆኑ አሰራሮችን እየነቀሰ በማውጣት ምቹና ሊያሰራ የሚችል  የህግ ማዕቀፎችን እያዘጋጀ ይገኛል። በዝግጅቱ ውስጥ አስፈፃሚው ተቋም፣ በህጉ የሚመራው የንግድ ማህበረሰብ እና ተጠቃሚው ማህበረሰብ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ የህግ ማዕቀፍ አስፈፃሚ ተቋማት ወስደው ተፈፃሚ እንዲሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ነው ቅንጅታዊ አሰራር የሚባለው፡፡

በዲጂታል አሰራር ውስጥ የህግ ማዕቀፍ፣ የማይቆራጥ የበይነ መረብ ግንኙነት፣ ገንዘብ እና ሌሎችንም የሚያቀርቡ ተቋማት በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሲሆን ነው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን የሚሆነው፡፡

ሰሞኑን በተጠና ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ የሞባይል አገልግሎት እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ቁጥር 119.3 ሚሊየን አድርጎ በተሰራው በዚህ ጥናት ውስጥ በኢትየጵያ 29.83 ሚሊየን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ ይህ ቁጥር ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥር 25 በመቶው ማለት ነው፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021 በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በ2022 በ731 ሺ ወይም በ2.5 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህ ማለት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ጭማሪ አሳየ እንጂ አሁንም 89.5 ሚሊየን ህዝብ ወይም 75 ከመቶው ከበይነ መረብ ግንኙነት ውጭ ነው።

በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 መከሰትን ተከትሎ በይነመረብን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ክስተት የበይነ መረብ ተጠቃሚውን ቁጥር ከዚህ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ይገመታል፡፡

በ2022 የበይነ-መረብ ግንኙነት ፍጥነት በኢትዮጵያ፡-

Ookla የታተመ መረጃ እንደሚያሳው ኢትዮጵያ ውስጥ የሞባይል የበይነ-መረብ ግንኙነት ፍጥነት 14 ሜጋ ባይት በሰከንድ፣ መካከለኛው ደግሞ 3.31 ሜጋ ባይት በሰከንድ ነው፡፡

በመረጃው መሰረት ይህ አሃዝ በ2022 መጨረሻ በኢትዮጵያ ያለው አማካይ የሞባይል የበይነ-መረብ ግንኙነት ፍጥነት በ2.08 ሜጋ ባይት በሰከንድ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም በ12 ወራት ውስጥ በ17.4 በመቶ ከፍ ብሏል ማለት ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቋሚ የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነት በ0.58 ሜጋ ባይት በሰከንድ (+21.2%) ጨምሯል።

በ2022 በኢትዮጰያ ያለው የሞባይል ግንኙነት፡-

ከጂ ኤስ ኤም ኤ ኢንተለጀንስ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በ2022 መጀመሪያ ላይ 58.54 ሚሊዮን የሞባይል ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች በስራ ምክንያት ከአንድ በላይ የሞባይል ስልክ ሰለሚይዙና ከበይነ መረብ ጋር ስለሚገናኙ በግለሰብ ደረጃ ይሄ ቁጥር ዝቅ ይላል፡፡ ይህ አሃዝ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 49.1 በመቶ ነው፡፡

ከ2021 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ያለው የሞባይል የበይነ መረብ ግንኙነት በ9.4 ሚሊዮን ወይም 19.2 በመቶ ጨምሯል።

የበይነ መረብ ግንኙነት ተጠቃሚዊች ቁጥር እያደገ ሲመጣ የኦንላይን አገልግሎትን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይመጣል። የኦንላይን ንግዶች ይስፋፋሉ፡፡ በዚያው ልክ ደገሞ በይነ መረብ ግንኙነት ፍላጎት እየጨመረ ይመጣል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook