በኢትዮጵያ የአምስተኛው ትውልድ የበይነ መረብ አገልግሎት መጀመር ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

5ኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎትየበይነ መረብ አገልግሎት ጅማሮ ሁለት ኮምፒውተሮች እርስ በእርስ እንዲገናኙና እንዲነጋገሩ ከማድረግ ሙከራ ነው የሚጀምረው፡፡ ከአንድ ኮምፒውተር ወደ ሌላ ኮምፒውተር መረጃ ለመለዋወጥ ሲደረግ የነበረ ምርምር አድጎ ነው ወደ በይነ መርብ ግንኙነት ያመራው። ቀደም ብሎ የተለያዩ ጥናቶች ሲካሄዱ ቢቆዩም የበይነመረብ ግንኙነት የውልደት ዘመን ተበሎ የሚጠራው 1983 ነው፡፡ ይህም በኮምፒውተሮች መካከል ወጥ የሆነ የኢንተርኔት ፕሮቶኮል በመፈጠሩን ምክንያት ነው፡፡

በ1960 የተለያዩ ኮምፒውተሮችን ለማገናኘት የተነሳው ሃሳብ አድጎ 1983 ላይ የስልክ መስመርን ከኮምውተር ጋር በማገናኘት በዓለም ላይ ያሉ ኮምፒውተሮች እርስ በእርሳቸው እንዲገናኙ እና በኢሜል እንዲነጋገሩ ማድረግ ተችሏል፡፡ HTML እና URL መፈጠር አለም አቀፍ ድር (world wide-www) ውልደት መነሻ መሆን ቻሉ፡፡ በ1995 ያሁ፣ ማይክሮሶፍት እና ኢቤይ፣ በ1998 ደግሞ ጉግል የበየነ መረብ ማሰሻዎችን በመፍጠር የበይነ መረብ ግንኙነትን እድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ አደረሱት፡፡ ከዚህ በኃላ የበይነ መረብ ግንኙነት እድገት ስሌት ፍጥነትና ተደራሽነት ላይ ወደ መሆን ተሸጋገረ፡፡አነዚህን የተለያዩ ደረጃዎች አልፎ ዛሬ የበይነ መረብ ግንኙነት አድጎ 5ኛው ትውልድ የበይነ መረብ ግንኙነት ላይ ደርሷል፡፡

5ኛው ትውልድ የበየነ መረብ ግንኙነት:-ይህ የበይነ መረብ ግንኙነት ዓለም ላይ በሙከራ ደረጃ ያለ ነው፡፡ የትኛውም ሀገር ይህንን ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ የተገበረ የለም፡፡ ከ4ኛው ትውልድ ቀጥሎ የመጣውና እጅግ ፈጣኑ ገመድ አልባ የበይነ መረብ ግንኙነት ሲሆን በዳታ ልውውጥ ፍጥነት ላይ የማይገመት ለውጥ ያመጣ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ መረጃ መሸከም የሚችልና ጠቅጥቅ ያለ/ አጯጭር የራዲዮ ሞገድ ይጠቀማል፡፡ የራዲዮ ሞገዶቹ አጭር ወይም የተጠጋጉ እንዲሆኑ የተደረጉት ትልልቅ መረጃዎችን መሸከምና ማስተላለፍ እንዲችሉ ነው፡፡ አነዚህን መረጃዎች መቀበል እና ማስተላፍ የሚያስችሉ መቀበያ መሳሪዎች ደግሞ በየቦታው ይገጠማሉ፡፡ መሳሪያዎቹ በራዲዮ ሞገድ አማካኝነት መረጃዎችን በመቀበልና በማስተላፍ መረጃን ከአንድ ወገን ወደ ሌላው ወገን በፍጥነት ለማስተላፍ ይጠቅማሉ፡፡

የ5ኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነትን ታሪካዊ በሆን ሁኔታ እየቀየረ ያለ ነው። ከዚህ በፊት የነበረውን የመረጃ ልውውጥ ፍጠነት በእጅጉ የሚያሻሻልና መረጃን ከአጠገባችን ካለ ሰው እጅ ላይ እንደመቀበል ቀላል የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ የበይነ መረብ ግንኙነት ትልልቅ መጠን ያላቸውን ዳታዎች በፍጥነት ለመለዋወጥ እድል የሚፍጠር ነው፡፡ ለምሳሌ ሁለት ሰዓት የሚፈጅን አንድ ፊልም ወደ ሞባይላችን ወይንም ወደ ኮምውተራችን ለማውረድ ብንፈልግ በ3ኛው ትውልድ ከ 40 እስከ 60ደቂቃ የሚፈጅ የነበረ ሲሆን በ 4ኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት ደግሞ 5 ደቂቃ ብቻ ይፍጃል፡፡ 5ኛው ትውልድ ይህንን የደቂቃ እርዝማኔ በእጅጉ አሳጥሮ ወደ 3.6 ሰከንድ አውርዶታል፡፡ ያ ማለት ሁለት ሰዓት የሚፈጅን ፊልም በ3ኛው ትውልድ የበይነ መረብ ግንኙነት ለማውረድ አንድ ሰዓት ገደማ ይፈጅ የነበረ ሲሆን በ5ኛው ትውልድ ግን በ3.6 ሰከንድ ማውረድ ይቻላል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ሁል ጊዜ በዚህ ፍጥነት መረጃዎችን ማውረድ እና መጫን ይቻላል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ በተለያዩ ተለዋወጭ ጉዳዮች የፍጥነት ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የተለያየ ትውልድ የበየነ መረብ ግንኙነቶች በተጠቀሰው ቁጥር መጠን የተቀመጠ አቅም አላቸው ማለት ነው።

5ኛው ትውልድ የበይነ መረብ አገልግሎት ለመጠቀም የምንጠቀማቸው መሳሪያዎች ይህንን ቴክኖሎጂ መቀበል የሚችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ስልኮች አሁን ባሉበት ደረጃ ይህንን ቴክኖሎጂ ማስጠቀም አይችሉም፡፡ ምናልባት ከ4ኛው ትውልድ ወደ 5ኛው ትውልድ መሸጋገሪያ ላይ ያለውን ኤል ቲ ኢ ሊያስጠቅሙ ይችላሉ፡፡ ልክ እንደ 4ኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት ሁሉ 5ኛው ትውልድ ኢንትርኔት አገልግሎት፣ አገልግሎቱ በተዘረጋበት አካባቢ ብቻ ነው የሚሰራው። ለምሳሌ ሰዎች ከቦታ በታ እየተንቀሳቀሱ በስልካቸው ኢንትርኔት ሲጠቀሙ ከ4ጂ ወደ 3ጂ አልያም ወደ 2ጂ እተለዋወጠ የሚያስቸግረው የኢንተርኔት አገልግሎቱ በዚያ አካባቢ የተዘረጋውን መነሻ አድርጎ ስለሚወስድ ነው፡፡ 5ኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎትም በተዘረጋበት አካባቢ ብቻ ነው ሊሰራ የሚችለው፡፡ የ5ኛው ትውልድ በይነ መረብ መቀበያ እና ማሰራጫ ባለበት ቦታ የምንጠቀማቸው ስልኮች እና ኮምፒውተሮች ራሳቸው ግንኙነቱን እየቀየሩ እንድንጠቀም ያግዙናል፡፡በዚህ ቴክኖሎጂ በርካታ የመቀበያ እና የማስተላለፊያ መሳሪያዎችን በየቦታው መግጠም ይጠይቃል፡፡ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ የሬዲዮ ሞገድ ስለሚጠቀም የተለያዩ ተፈጠሯዊ እና ሰው ሰራሽ ነገሮች ለግንኘነቱ እንቅፋት ሊሆኑበትም ይችላል፡፡

ቴክኖሎጂው ለዲጂታል አሰራር ያለው ፋይዳ፡-

ዓለም ወደ ዲጂታል አሰራር እየገባ ነው፡፡ በወረቀት የሚሰጡ አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ እየተቀየሩ ዲጂታይዝ ሆነዋል፡፡ በወረቀት የነበሩ መረጃዎች ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ እየተደረጉ ነው፡፡ የባንክ ስርዓት፣ ንግዶች፣ አገልግሎቶች እና መረጃ ልውጦች ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል አሰራር እየተቀየሩ ነው።ኢትዮጵያ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን ቀርፃ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ ዲጂታል ስትራቴጂው ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች አንዱ የበይነ መረብ ግንኙነት ነው፡፡ የበይነ መረብ ግንኙነት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ ዲጂታል ፋይናንስ፣ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት፣ ኢ ኮሜርስ እና የመሳሰሉት ካለ ፈጣን የበይነ መረብ ግንኙነት የማይታሰቡ ናቸው፡፡አሁን አብዛኛው ሰው የእለት ከእለት እንቅስቃሴው ከበይነ መረብ ጋር ተገናኝቷል፡፡ ባንከ ካለ ኢንተርኔት አይታሰብም፣ አብዛኞቹ የመንግስት አገልግሎቶች ኦንላይን ሆነዋል፡፡ የንግድ ልውውጦች በዲጂታል መልኩ እየተፈፀሙ ነው፡፡ ሰዎች ከፍተኛ መረጃ የሚለዋወጡት በይነ መረብን በመጠቀም ነው፡፡ የበይነ መረብ ፍጥነት መሻሻል ደግሞ እነዚህ አገልግሎቶች በተቀላጠፈ መልኩ እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡በኢትዮጵያ የአምስተኛው ትውልድ የበይነ መረብ አገልግሎት መጀመር ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook