የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከ አይ ሲቲ ኢቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ዲጂታል ፋይናንስ ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱን የከፈቱት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ቁልፍ የሆነውን የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት ማዘመን ላይ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዘርፉ እንዲነቃቃ የማስፈፀሚያ መመሪያና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
የብሄራዊ ባንክ የክፍያ ስርዓት ክትትልና ልማት ዋና ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዳምጠው የዲጂታል ክፍያዎችን ለመፈፀም የሚያስችሉ ስርዓቶችን ለመዘርጋት መደላድሎች በመፈጠራቸው ዘርፉ መነቃቃት እያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።
አሁን እየተሰራበት ያለው የወረቀት ገንዘብ ልውውጥ ባለበት መቀጠል እንደማይቻል ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል። የኦንላይን ክፍያ ለመፈፀም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ተደርጓል ያሉት ሃላፊው ከመረጃ መረብ ደህንነት ጋር በተያያዘም ትልቅ አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል።
የኢት ስዊች ዋና ስራ አስፍፃሚ አቶ ይለበስ አዲስ ከአካውንት ወደ አካውንት፣ ወደ ዋሌት እና ወደ ሌሎች ባንኮች ገንዘብ ማስተላለፍና በጥቅሉ የኦንላይን ባንኪንግ ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን አብራርተዋል።
የሞኔታ ቴክኖሎጂ ስራ አስኪያጅ አቶ የምሩ ጫንያለው በአሞሌ ክፍያ በኩል ከ2 ሚሊየን ተጠቃሚ ወደ 7.3 ቢሊየን ብር እንደሚዘዋወር አብራርተዋል። የስፖርት ውድድር መግቢያ ትኬት፣ የትምህርት ቤትና የመዝናኛ ክፍያ በአሞሌ በኩል እንደሚፈፀሙና በቀጣይ ኢ-ኮሜርስና ኢ-ማድረስ (E- delivery) ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የንግድ ባንክ የመረጃ ስርዓት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማረ አሰፋ የዲጂታል ክፍያ ተደራሽነትን ለማስፋትና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን እስከ ገጠር ድረስ ለማውረድና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅሳቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በውይይቱ ከ250 በላይ የዘርፉ ተዋናዮች እና ተሳታፊዎች ተካፍለዋል።