ስልጠናው የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የዳታ ሳይንስ ቡድን ጋር በመተባበር የተሰጠ ነው። ከፍተኛ የዳታ ሳይንስና ምልከታ (Advanced data Science and Visualization) መስክ በዓለም በቅርብ ጊዜ ከተጀመሩት መስኮች አንዱ ሲሆን፣ ሀገራችንም ለጀመረቻቸው የተለያዩ የትኩረት መስኮች ውጤት የሚያግዝ መሆኑ ታምኖበት የተሰጠ ነው።
ዘርፉ በተለይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ስኬት እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎ መስክ አቅም በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የከፍተኛ የዳታ ሳይንስና ምልከታ እውቀት አሁን ላለንበት የመረጃ ዘመን ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ተመራቂዎቹ ባገኙት እውቀት የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
ለ3 ወራት በበይነ መረብ በተሰጠው ስልጠና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከመንግስት መሥሪያቤቶች፣ በዘርፉ ከተሰማሩ የግል የቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲሁም ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች (Startups) የተውጣጡና መመዘኛውን ያለፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ስልጠናው ሀገራችን ለምታደርገው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተሰጠ ሲሆን ሰልጣኞቹ በዘርፉ ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ያስችላቸዋል።