በዓለም በቅርብ ጊዜ ከተጀመሩት መስኮች ውስጥ አንዱ የሆነው “ከፍተኛ የዳታ ሳይንስና ምልከታ” ላይ ያተኮረ ስልጠና በኢትዮጵያ መስጠት ተጀመረ።

ስልጠናው የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የዳታ ሳይንስ ቡድን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

ከፍተኛ የዳታ ሳይንስና ምልከታ (Advanced data Science and Visualization) መስክ በዓለም በቅርብ ጊዜ ከተጀመሩት መስኮች አንዱ ሲሆን፣ ሀገራችንም ለጀመረቻቸው የተለያዩ የትኩረት መስኮች ውጤት የሚያግዝ መሆኑ ታምኖበት የተዘጋጀ ነው።

ስልጠናው ሀገራችን ለምታደርገው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎም ተለይቷል።በተለይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ስኬት እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎ ዘርፍ አቅም በመገንባት ረገድ አስተዋዕጾው ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ባዩ (ፒ ኤች ዲ) በስልጠናው መከፈቻ ላይ “ስልጠናው ኢትዮጵያ በዘርፉ የሰለጠኑ ሰዎች እንዲኖራትና ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት በቀለ (ፒ ኤች ዲ) በኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ስልጠና ሲሰጥ የመጀመሪያው እንደሆነና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሰጥ ተናገዋል።

በበይነ መረብ የሚሰጠው ስልጠና ለዐሥር ተከታታይ ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከመንግስት መሥሪያቤቶች፣ በዘርፉ ከተሰማሩ የግል የቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲሁም ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች (Startups) የተውጣጡና መመዘኛውን ያለፉ 55 ሠልጣኞች ይሳተፉበታል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook