በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ልማት ቋሚ ኮሚቴ እና የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተቋሙን ጎብኝቷል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክሪስቲያን ታደለ የወጣቶቻችንን ህልም እውን ለማድረግና የፈጠራ ስራዎቻቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ተቋሙ ጉልህ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሳይንሱም ሆነ በፈጠራው የጀግኖች ሀገር መሆኗን ለአለም የምታመሰክርበት ተቋም ነው ያሉት ሰብሳቢው ልዩ ችሎታን ብቻ ሳይሆን ልዩ ፍላጎት ያላቸውንም ታሳቢ ያደረገ መሆን አንዳለበት ተናግረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ስራ ክህሎት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶር ከይረዲን ተዘራ ተቋሙ ከዩኒቨርስቲዎች፣ ከአንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትስስር በመፍጠር መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፈጠራ ሀሳቦችን ሰብስበን ወደ ተግባር የምንቀርበት ተቋም እንጂ የፈጠራ እውቀት ችግር የለም ያሉት ምክትል ሰባሳቢው ይህንን ችግር ለመፍታት ተቋሙ በፍጥነት ወደ ስራ መግባት አለበት ብለዋል፡፡
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) ይህ ፕሮጀክት በሀገራችን በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ገብተው የሚማሩበት ሲሆን ይህም ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥናል ብለዋል።
ከፕሮጀክቱ የሚገኘውን ልምድ በቀጣይ በክልሎችም ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ተቋም በ2015 በጀት ዓመት 500 ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማር ስራውን የሚጀምር ሲሆን በቀጣይም 1000 ተማሪዎችን የመቀበል አቅም አለው።