ብሎክቼን፣ ዲጂታል ገንዘብ እና ዲጂታል ግብይት

ዲጂታል ግብይት ማለት የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ እቃ መግዛትና መሸጥን በዲጂታል መልኩ ማስኬድ ማለት ነው። በመሸጥና በመግዛት ሂደት ውስጥ በኦንላይን ግብይት ከፍያን በተለያዩ የክፍያ አማራጮች ከወረቀት ነፃ በሆነ መልኩ መፈፀም ነው።

የዲጂታል ገንዘብ  ከወረቀት ገንዘብ በመውጣት የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም ሊታይ እና ሊዳሰስ የማይችል ምናባዊ ገንዘብ መፍጠር ማለት ነው። ይህ የገንዘብ አይነት ገና ወደ አንድ ስምምነት የተመጣበት አይደለም።

ብሎክቼን እና ዲጂታል ገንዘብ

በዓለም ላይ የሚፈጠሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ በእጅጉ እየቀያየሩት ይገኛሉ። በተለይ ዲጂታል ቴክኖሎጂው መሰፋፋት በተለምዷዊው አሰራር መጓዝ ለሚፈልጉት ፈተና እየሆነባቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ሳይወዱ በግድ ቴክኖሎጂው በራሱ ጊዜ ይዟቸው ይጓዛል፡፡ ካልሆነ ግን ከውድድር ውጭ መሆን ነው።

በአሁኑ ጊዜ የፋይናንስ ስርዓቱ ወደ ዲጂታል አሰራር እየተቀየረ ነው። የወረቀት ብር ዝውውር በእጅጉ እቀነሰ በዲጂታል መልኩ ክፍያ እና ግብይት እየተፈፀመ ከፍ ሲል ደግሞ የዲጂታል መገበያያዎች እየተፈጠሩ ነው። የገንዘብ ዝውውር በአጭበርባሪዎች አይን ውስጥ ሰለሚገባ በከፍተኛ ደረጃ ቁጥጥር እና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው።

ለዚህ ነው የቴክኖሎጂ ባለሙያች ፊታቸው ወደ ብሎክቼን እና የዲጂታል ገንዘብ እያዞሩ ያሉት።

ጥብቅ ሰንሰለት (ብሎክ ቼይን) ምንድነው? የተቀመረ (የዲጂታል) ገንዘብስ?

በአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ በመካከል አገልግሎቱን የሚሰጥ የታመነ አንድ አካል ይኖራል። ለምሳሌ በገንዘብ ዝውውርና ቁጠባ ውስጥ ባንክ የሚባል የታመነ ተቋም አለ። በመሬት አሰተዳደር ውስጥ ደግሞ መንግሰት ያቋቋመው መሬት አስተዳደር ወይ ደግሞ ሌላ ስም የተሰጠው መስሪያ ቤት ይኖራል። ባንኮች ከደንበኞቻቸው ገንዘብ በመቀበል ያስቀምጡላቸዋል። ገንዘብ ያዘዋውሩላቸውል። ግብይት እንዲፈፀሙ ያደርጓቸዋል።  ደንበኛው ባንኩን ስለሚያምን ገንዘቡን ያስቀምጣል።

በመሬት አሰተዳደር ውስጥ ደግሞ ዜጎች የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫቸውን መንግስት ይሰጣቸዋል። መሬታቸውን በማስመዝገብና በማስተዳደር መካከል መንግስት ያቋቋመው አንድ ተቋም አለ። እነዚህ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ደንበኞቻቸውን ማጭበርብር ቢፈልጉ ሊያደርጉት ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ 10 ሄክታር ያለው አርሶ አደር መሬት አስተዳደር ውስጥ ያሉ ሰዎች 2ቱን ሄክታር ለሌላ ሰው አስተላልፈው 8 ሄክታር ነው ያለህ ሊሉት ይችላሉ። ወይንም አንድ መኖሪያ ቤት ያለውን ሰው መረጃዎቹን በማጥፋት ሰሙን በሌላ ሰው አዙረው ቤት የለህም ብለው ሊያጭበረብሩት ይችላሉ።

የጥብቅ ሰንሰለት ቴክኖሎጂ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና በሶስተኛ ወገን ያሉ አካላትን ከመካከል ለማውጣት እቅድ ያለው ቴክኖሎጂ ነው። ያ ማለት በማይሳሳት፣ በማይሰረዝ እና በማይጭበረበር በሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በማይዘረፍ ስርዓት መተካት ነው።

ጥብቅ ሰንሰለት ወይም ብሎክቼን በሚሊየን የሚቆጠሩ የኮምፒውተር መረጃዎችን ባልተማከለ መልኩ የሚመዘግብ የብሎክ ጥርቅም የሆነ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በባንኮች እጅ የሚገኘውን እና በመንግሥታት ግምጃ ቤት ቁጥጥር የሚደረግበትን የገንዘብ ዝውውርና የመረጃ ፍሰት ያልተማከለ ለማድረግ እቅድ አለው። ከዚህ በተጨማሪ ከገንዘብ ዝውውር እስከ የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ ያሉ ሥራዎችን ሊከወንበት እንደሚችል ተስፋ የተጣለበት አዲስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡

መረጃዎች በሁሉም ኮምፒውተሮች ተመዝግቦ ስለሚገኝ በጭራሽ የማይሳሳት፣ የማይሰረዝ እና የማይጭበረበር በሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የማይዘረፍ የአሰራር ሥርዓት ያለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ለምሳሌ አንድ ሰው በዲጂታል መልክ ያለውን የገንዘብ መጠን ላይ አንድ ዜሮ ጨምሮ መጠኑን ከፍ ለማድረግ ሙከራ ቢያደርግ ዓለም ላይ ያሉ ኮምፒውተሮች ላይ መረጃው ሰለሚመዘገብ ኮምፒውተሮቹ ማጨበርበሩን ይነግሩትና ውድቅ ያደርጉበታል።

ይህ ቴክኖሎጂ በተለይ በአፍሪካ ምድር አጨቃጫቂና የግጭት መንስኤ የሆነውን የመሬት አስተዳደርን በመመዝገብ ችግሩን ይፈታል ተብሎ ይታመንበታል፡፡ በጥብቅ ሰንሰለት (በብሎክ ቼይን) ቴክኖሎጂ የተመዘገበ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ደግሞ በሁሉም ኮምፒውተሮች ተመዝግቦ ስለሚገኝ በኃላፊዎችና በሰራተኞች ከሚደርስበት መጭበርበርና ከሶስተኛ ወገን ስርቆት ይገጥመዋል ተብሎ የማይሰጋበት ከስርቆት የፀዳ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው መኪና ገዝቶ ክፍያውን በዚህ ቴክኖሎጂ  ቢፈፅምና ሻጩ አልሰጠኝም ብሎ ቢክድ ዓለም ላይ ኮምፒተሮች ለገዢው ምስክር ሆነው ይቆማሉ።       

በብሎክቼይን የተመዘገበ አንድ መሬት በሙስና ለሌላ ሰው ቢተላለፍ መረጃው ኮፒ ሆኖ በአለም ላይ ባሉ ኮምፒውተሮች ስለሚቀመጥ የትም ቦታ ላይ ይህ ስራ እንደተሰራ ስለሚነግረን ሙሰኞችን ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡ ከአፍሪካ ውስጥ ሩዋንዳ ወደዚህ ቴክኖሎጂ በመግባት የመሬት አያያዝን ለማዘመን በቴክኖሎጂው ባለሙያዎች ጋር ስምምነት ተፈራርማ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምራለች፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ የብሎክቼን ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ብቻ የተሳተፉበትን ቡድን አሰልጥና አስመርቃለች። እነዚህ ሴቶች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። ይህም ኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ ዝውውር ስርዓት ውስጥ ዲጂታላይዝ የሆነ ስርዓትን ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍ ነው፡፡

ብሎክ ቼይን የተሳካና ግልፅ የሆነ ምርጫም ለማካሄድ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ለዲጂታል መታወቂያ፤ የማንፈልጋቸውን መረጃዎች ሙሉ ለሙሉ ለመሸጥ፤ የቅጅ መብትን ለማስጠበቅ፤ ለቤቶች አስተደዳር፤ የእቃ ዝውውርን ለማከናወን፤ ለግብር መክፈያ፤ ለህክምና ስራ (የታካሚዎችን መረጃ ለመያዝ እና ለመሳሰሉት)፤ ለህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር ቁጥጥር፤ እና ለመሳሰሉት ጥቅም ላይ የሚውል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

የተቀመረ ገንዘብ (ዲጂታል ገንዘብ) ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ ምንድነው?

የቴኖክሎጂ ባለሙያዎችን እስከ ዛሬ ሲያስጨንቃቸው የነበረው ጉዳይ አንድን እቃ ቅጂው እጃቸው ላይ ሳይኖር ለሌላ ሰው እንዴት ማስተላለፍ ይቻላል? የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ 50 ብርን ለአንድ ሰው በዲጂታል መንገድ ለመላክ ኮፒው ላኪው ጋር አለመቅረቱ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ይህ ጉዳይ ክሪፕቶግራፈሮች ለረጅም ጊዜ ሲቸገሩበት የነበረው ጉዳይ ነው፡፡ ክሪፕቶ ከረንሲ ይህንን ችግር የፈታና የዲጂታል ገንዘብ ቅጂው ላኪው ጋር ሳይቀር መላክ የሚያስችል አዲሱ ቴክሎጂ ነው፡፡

የጥብቅ ሰንሰለት ቴክኖሎጂ ወይም ብሎክቼን የዲጂታል ገንዘቦችን (ምናባዊ ገንዘብ) ይጠቀማል። ለምሳሌ አለም ላይ ብር፣ ዶላር፣ ዩዋን የሚባሉ የወረቀት መገበያያ ገንዘቦች እንዳሉ ሁሉ ቢትኮይን፣ ኢቲሪየም፤ ኢቲሪየም ካሽ፤ ዳሽ፤ ዚካሽ የሚባሉ የዲጂታል ገንዘቦች አሉ።

በተለመደው አሰራር የሀገራት የገንዘብ ዝውውር መንግስት እና ባንኮች የሚቆጣጠሩት ነው፡፡ ቢትኮይን የተባለው ገንዘብ ግን ዝውውሩን የሚቆጣጠረው ባለቤቱ ሲሆን የዝውውሩ ህጋዊነት ማረጋገጫ ደግሞ ሁሉም የቢትኮይን ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ሰዎች በአለም ላይ ካሉ ከሚፈልጉት ሰው ጋር በየትኛውም ቦታ ሆነው ሶስተኛ ወገን ወይም ባንክ ሳያስፈልግ የሚገበያዩበት ቴክኖሎጂ ነው።  ማንም ሊቆጣጠረው እና ሊያጭበረብረው አይችልም፡፡ መንግስታትም ቢሆኑ፡፡ ቁጥጥሩ በሁሉም ግልሰቦች እጅ ሆኖ በሁሉም የቢትኮይን ረቂቅ ገንዘብ ተጠቃሚ ኮምፒውተሮች ላይ መረጃዎቹ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው የቢትኮይን ተጠቃሚ ሲሆን ልክ እንደ ጂ-ሜል እና ፌስ ቡክ የመለያ ስም አውጥቶ የሚስጥር ቁልፍ መርጦ መጠቀሚያ ይከፍታል፡፡ የሚስጥር ቁጥሩ በጣም ጠንካራ በመሆኑ የመሰረቅ አደጋ አይገጥመውም፡፡ ከዚያ ከፈለገው ሰው ጋር ቢትኮይን መላላክ ይችላል፡፡ ያ የተላላከው የገንዘብ ዝውውር በአለም ላይ ባሉ ኮምፒውተሮች ቅጂው ይቀመጣል፡፡ እነዚህ ሁለት ሰዎች ቢከዳዱ እንኳ አለም ላይ ባሉ ኮምፒውተሮች ዝውውሩ ተመዝግቦ በቅጂ መልክ ስለሚቀመጥ እውነቱን ማወቅ ይቻላል፡፡

በቀላል ምሳሌ እንየው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ጫማ መግዛት ቢፈልግ እና ባንክ ቤት ገንዘብ ለማውጣት ቢሄድ ባንክ ቤቱ ሰውየው በስሙ ገንዘብ መኖርና አለመኖሩን አረጋግጦ ገንዘብ ይሰጠዋል፡፡ ሰውየው ገንዘብ እንዳለውና እንደሌለው የሚያውቀው ባንኩ ብቻ ነው፡፡ እሱን ካረጋገጠ በኋላ ገንዘቡን ይሰጠውና የሚፈልገውን መግዛት ይችላል፡፡

ሰውየው በክፍያ ካርድ ቢሆን መግዛት የሚፈልገው እና ካርዱን ለባለሱቁ ሰጥቶ የጫማ መግዣውን ቢያስቆርጥ፤ ሰውየው ገንዘብ እንዳለውና እንደሌለው የሚቆጣጠረው በተመሳሳይ ሶስተኛ ወገን የሆነው ባንኩ ነው፡፡

ወደ ቢትኮይን ሰንመጣ  የቢትኮይን መጠቀሚያ ያለው ሰው እቃ ገዝቶ የመገበያያ ገንዘብ ወይም ቢትኮይን እንዳለውና እንደሌለው የሚቆጣጠሩት አለም ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ቢትኮይን የሚተላለፍለት ሰው ቢትኮይን አለው ወይ ብሎ ሲጠይቅ አለም ላይ ያሉ ኮምፒውተሮች በቂ ቢትኮይን ካለው ‹‹አዎ›› ከሌለው ደግሞ ‹‹የለውም›› ብለው ማረጋገጫ ይሰጡታል፡፡ ክፍያው ከተፈፀመ በኋላ ደግሞ ቅጂው በመላው አለም ላይ ባሉ ኮምፒውተሮች ተሰራጭቶ ይቀመጣል፡፡

ክፍያው ሲፈፀም ግልባጩ አልያም ቅጂው በዓለም ላይ ባሉ ኮምፒውተሮች የሚቀመጠው በሚስጥራዊ ስም ነው፡፡ እንጂ በተገልጋዩ የመጠሪያ ስም አይደለም፡፡ ከመጀመሪያው የቢትኮይን መጠቀሚያ ሲከፈት ሚስጥራዊ ኮድ አብሮ ይፀድቃል፡፡ ያ ምስጢራዊ መጠቀሚያ ማንም የማይከፍተውና ሊያጭበረብረው የሚችል አይደለም፡፡ የመገበያያ ገንዘቡ ለዚያ ነው ረቂቅ አንዳንዶችም ምናባዊ የሚሉት፡፡

ምንዛሬውስ?

ከእነዚህ ዲጂታል ገንዘቦች ውስጥ ቢትኮይን ከፍተኛ ዋጋ ያለው የብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ቢትኮይን በፈረንጆች 2008 ሳቶሺ ናከሞሮ በተባለ ሰው የተፈጠረ ምናባዊ የመገበያያ ገንዘብ ነው፡፡ ይህ አዲስ ዋጋ ያለው ገንዘብ አለም አሁን እየተጠቀመባቸው ካሉ ገንዘቦች ሁሉ በምንዛሬ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ረቂቅ ገንዘብ ነው፡፡ የቢትኮይን ዋጋ በየጊዜው ይጨምራል፡፡ የተወሰነ መዋዠቅም ያጋጥመዋል፡፡ ለምሳሌ ግንቦት 2010 ላይ የ1 ቢትኮይን ዋጋ 0.01 ዶላር ነበር፡፡ ታህሳስ 2017 የ1 ቢትኮይን ዋጋ 19ሺ 783 ዶላር ደረሰ፡፡ የካቲት 2021 ላይ አንድ ቢትኮይን 60ሺ ዶላር ገብቶ ነበር። ዛሬ ግንቦት 23/ 2014 አንድ ቢትኮይን 31,561.13 ዶላር ነው።  

የቢትኮይን ገንዘብ ከፍተኛ ዋጋ አውጥቶ የነበረው እነ ቴስላ በቢትኮይን ላይ ከፍተና ገንዘብ በማፍሰሳቸው ነበር። ባለሃብቶች ቢትኮይንን መግዛት ሲጀምሩ እና የተለያዩ ተቋማት ግብይት በዚህ ዲጂታል ገንዘብ መፈፀም ሲጀምሩ ዋጋው እየጨመረ ይሄዳል።

የብሎክቼን አልሚዎች፡-

የብሎክቼን አልሚዎች (Blockchain miners) በጥብቅ ሰንሰለት ቴክኖሎጂ ውስጥ የሚዘዋወሩ የዲጂታል ገንዘቦችን ዝውውር የሚቆጣጠሩ እና የሚያዘምኑ ናቸው። በዓለም ላይ ባሉ ኮምፒውተሮች ውስጥ የተመዘገቡ መረጃዎች እና የተዘዋወሩ የዲጂታል ገንዘቦችን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ናቸው። ይህ ስራ በግል እና በቡድን ሊሰራ ይችላል። ብሎክቼንን በማስተዳደር ረገድ ግን ዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ መብት አላቸው። ዝውውሩን ለማረጋገጥ ደግሞ ከፍተኛ አቅም ያለው ኮምፒውትር ያላቸው ማይነሮች ይሳተፋሉ።

የዲጂታል ገንዘብ የሚነሳበት ተቃውሞ፡-

የዲጂታል ገንዘብ መንግስታት/ባንኮች/ ቁጥጥር ሰለማያደርጉበት ወንጀልን ሊያስፋፋ ይችላል ተብሎ ይሰጋል። ችግር ተፈጥሮ መንግስታት የገንዘብ ዝውውር እገዳ ለመጣል ቢፈልጉ ይህ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፡፡ ነገር ግን ለሌሎች ዘርፎች የብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።

አሜሪካ፤ ካናዳ፤ ፊንላንድና ቤልጂየም በተለያየ መልኩ ቢትኮይንን የተቀበሉት ሲሆን ቻይና፤ ሩስያ፤ ቬትናምና ቦሊቪያ ደግሞ እገዳ የጣሉ ሀገራት ናቸው፡፡ ነገር ግን የሀገራት አቋም በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀያየርበት ጊዜ አለ።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook