የግብርና ሚኒስቴር በግብርናው ዘርፍ የዲጂታል አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያስችለውን “የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽ አና ማማከር ስትራቴጂ” ለማዘጋጀት በአዲስ አበባ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው።
የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴን (ፒ ኤች ዲ) የዲጂታል ግብርና ኢክስቴንሽንና የማማከር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ በግብርናው ዘርፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጋል ብለዋል።
ፍኖተ ካርታው የዲጂታል መፍትሄዎችን በማምጣት፣ የሳተላይት መረጃ በመጠቀምና ከፍተኛ ዳታ ትንተና በመስራት አርሶ አደሮች በቂ መረጃ እንዲያገኙ፣ ምርትና ምርታማናታቸውን እንዲያድግና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተቋማት የየዘርፋቸውን የዲጂታል ስትራቴጂ ሲነድፉ ከኢትዮጵያ ዲጂታል ስትራቴጂ 2025 ጋር በተጣጣመ መልኩ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።

የዲጂታል ስትራቴጂው ቅድሚያ ከሰጣቸው መስኮች ውስጥ የግብርናው ዘርፍ አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ግብርና በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰው ሃይል የተሸከመና የውጭ ምንዛሬ ማግኛ እንደመሆኑ መጠን የዲጂታል አሰራር ዝርጋታ ላይ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል።
በግርብርናው ዘርፍ አዳዲስ የዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት ምርታማነትን መጨመር፣ የምርት ስርጭትን ማቀላጠፍ፣ የስራ እድል መፍጠር እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ ይገባል ተብሏል።