አለም ዓቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ጉባኤ ፍጹም አፍሪካዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች፡፡

ጥሪው የቀረበው በበይነ መረብ አማካኝነት በተካሄደውና የአፍሪካ አህጉር ለአለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ኮንፈረንስ ቅድመ ዝግጅት ላይ ባተኮረው ስብሰባ ላይ ነው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ከፍተኛ አማካሪ መስፍን በላቸው (ፒ ኤች ዲ) ኢትዮጵያን በመወከል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር  የአፍሪካ ሀገራት በዝግጅቱ መነሳት ያለባቸውን አህጉራዊ አጀንዳ በማቅረብና በማዳበር ከሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ ባለፈ ከአዘጋጅዋ ሀገር ኢትዮጵያ ጋር በቅርበት በመስራት የዝግጅቱ ባለቤት መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኮንፈረንሱ አፍሪካዊ እሴቶችን እንዲያስተዋውቁና ኮንፈረንሱን ፍጹም አፍሪካዊ ለማድረግ እንዲተጉ ጠይቀዋል፡፡

በአፍሪካ ያለው የቴክኖሎጂና የኢንተርኔት ግንኙነት ስፋትና ስርጭት ደካማ መሆን የአህጉሪቷን ልማት ሲጎትት መቆየቱን ያስታወሱት አማካሪው አሁን ከተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ነባር ፈተናዎች መባባሳቸውንና አዳዲስ ችግሮች መወለዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

“በቀጣይ አመት በሚደረገው ኮንፈረንስም ዓለማቀፋዊ የሆኑትን ብቻ ሳይሆን አህጉራዊ ፈተናዎችና እድሎች የሚለዩበትና ለመፍትሄውም ከአለማቀፉ  ማህረሰብ ጋር በጋራ የምንሰራበት ሊሆን ይገባል” ብለዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኮንፈረንስ እያደረገች ያለውን ዝግጅት በዝርዝር ለአፍሪካ አባል ሀገራት አቅርባለች፡፡

ከከተማ ርቀው የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የኢንተርኔት ግንኙነት ስለሚያገኙበትና የአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚያግዙ ፈንድ የተመለከቱ ጉዳዮች በዋናው ኮንፈረንስ ላይ አብይ አጀንዳ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ ሃሳብ አቅርባለች፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook