የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አካባቢ ለሚኖሩ በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች የአዲስ ዓመት በዓል መዋያ ስጦታ አበርክቷል።
በስጦታ ፕሮግራሙ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
“ርቀታችንን ጠብቀን እየተረዳዳን ወደ አዲስ ዓመት እንዘልቃለን!” በሚል መሪቃል ጳጉሜ 5/2012 ዓ.ም በተዘጋጀው የበዓል ስጦታ ፕሮግራም ዘይት፣ ስኳር፣ እና ዱቄት ለችግረኛ ቤተሰቦቾ ተበርክቶላቸዋል።
የኢኖቬሽኖና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሐም በላይ (ዶ/ር) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትና የሚያደርገውን ልዩ ድጋፍ ከማጠናከር ጎን ለጎን በአገር ደረጃ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ቀን ከሌት ሰርተን የሕዝባችንን ኑሮ ለመቀየር ጥረታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
አዲሱ አመት የሰላም፣ የደስታና የብልፅግና አመት እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከ2010 ዓመት ጀምሮ በወረዳ አንድ የሚገኘውን የጆን ኤፍ ኬኔዲ የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ተከታታይ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡
በትምህርት ቤቱ ለሚማሩ በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ተማሪዎችን ዓመታዊ የምገባ ፕሮግራም እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፤ ለትምህርት ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ የመጸዳጃ ቤት፣ የሻወርና የአጥር ግንባታ ስራዎችን አከናውኖ አስረክቧል።
በቀጣይም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሞከረውን የተቀናጀ የከተማ ግብርና ፕሮጀክትን በፓይለት ደረጃ በትምህርት ቤቱ ለመጀመር እቅድ ተይዟል።