የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ ICT ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ኢንጅነር አብዮት ሲናሞ ዛሬ የብሔራዊ ዳታ ማአከልን ለሚዲያና ፕረስ አገልግሎት የስራ ክፍል በማስጎብኘት በማዕከሉ ስለሚሰጡ አገልግሎቶች ገለጻ አድርገዋል።
እንደ ዶክተር አብዮት የመንግስት አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ አግባብ ለማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች በዘርፉ እየተሰራ ነበር።
እስከዛሬ የለሙ አገልግሎቶችን በማስፋትና አዳዲስ ዘዴዎችን በመጨመር የመዋቅር ለውጦችን በቀላሉ ለማስተናገድ እንዲቻል ከ400 በላይ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች ተዘጋጅተዋል። ዶክተር አብዮት አክለውም የተዘጋጁት አገልግሎቶች ከ40 በላይ የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን የአሰራር ሂደት ለውጦችን በቀላሉ በማካተት ተግባራዊ ማድረግ በሚያስችል ቴክኖሎጂ ታግዘው ለመተግበርም የተዘጋጁ ናቸው።
የለሙት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች በሚታጠፉና አዲስ በሚደራጁ የመንግስት ተቋማት የነበሩ የአሰራር ሂደቶችን በፍጥነት በማቀናጀት አገልግሎቶቻቸውን ለማስቀጠል የሚያስችሉና ወጭ ቆጣቢ ናቸው።
እንደ ዳይሬክተር ጀነራሉ አገልግሎቶቹ በሚያስፈልጋቸው የባንድዊድዝ መጠን የተደገፉ እንዲሆኑ የወረዳኔት የባንድዊድዝ መጠንን በ 10 እጥፍ ከፍ በማድረግ ከ 2Gbps ወደ 20Gbps ማሳደግ ተችሏል::
ዘርፉ መስከረም 24/2014 የሚመሰረተው አዲሱ መንግስት በሚያቋቁማቸውና በሚያደራጃቸው ተቋማት የማህበረሰብ አገልግሎቶች በፍጥነት እና በጥራት ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ አገልግሎቶችን በሚፈለገው የ ICT መሰረተ ልማት እና ሲስተሞች ለመደገፍ አስተማማኝ ዝግጅት አድርጓል።
ዶክተር አብዮት በቀጣይ የሚደራጁ አዲስም ሆኑ ነባር ተቋማት ለመሰረተ ልማት ዝርጋታም ሆነ ለመሰል ሲስተምች ልማት ምንም ዓይነት ተጨማሪ ሀብት ወጪ ሳያደርጉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር የሚገኘውን የብሔራዊ ዳታ ማአከል መሰረተ ልማት እንዲጠቁሙ ጥሪ አቅርበዋል::