አገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎችና የስታርታፖች/ Startups/ መድረክ ተካሄደ!!!(የኢኖቬሽን ምርምር ድጋፍ ማመልከቻና ማሳወቂያ ፓርታልም ተመርቋል)

ጥር 26/2014 ዓ.ም

የአገር አቀፍ የፈጠራ ባለሙያዎችና የስታርታፖች/ Startups/ መድረክ በኢንተር ሌግዠሪ አዲስ ሆቴል ተካሂዷል። መድረኩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) በንግግር ከፍተውታል።

ክቡር ሚኒስትሩ በንግግራቸው በቴክኖሎጂ ዘርፍ ስራ ፈጣሪና ሃብት አመንጭ ለሆኑ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጣራዎችና እምቅ አቅምና ክህሎት ላላችው ድጋፍና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልፀዋል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በሀብት ማመንጨትና በስራ ፈጠራ ዘርፍ ብዙ ስራ የሚጠብቃቸው ሀገራት የነገ እድገታቸው የተሳካ ይሆን ዘንድ ዛሬ ላይ ለጀማሪ ቢዝነሶችና ለቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪወች (innovators) በሚሠጡት ድጋፍ፣ ማበረታቻና ጥበቃ የተመሠረተ መሆኑን አስምረው በመላ ሀገሪቱ ቴክኖሎጂና ፈጠራን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች ላይ በስፋትና በቀጣይነት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ምርምር እንድሁም ለስታርታፕ ድጋፍ ማመልከቻና ማሳወቂያ ፓርታል/ Ethiopia Startups and Innovation & research support portal/ አገልግሎትንም መርቀው አስጀምረዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የምርምርና ኢኖቬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒኤች ዲ) በበኩላቸው የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አንዱና ዋና ተግባሩ የፈጠራ ሀሳብን እና እኖቬሽንን ማበረታታት፣ መደገፍ እና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚና የፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶች ሐሳባቸውን ወደ እሴትና ምርት እንዲለወጡ በማድረግ ለሀገራዊ ብልጽግና የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑን ስለሚገነዘብ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ ተግባር መሳካት ስታርታፖዎች፤ ኢኖቬተሮች እና ኧንተርፕረነሮች ዋና ተዋናይ ናቸው ያሉት ሚኒስቴር ዲኤታው የኢንኩቤሽን ማዕከላት፣ አክሲለረተሮች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍና የመንግስት ተቋማት ተቀናጅተው አጠቃላይ የኢኖቬሽን ስርዓተ-ምህዳር እንዲፈጠር ገንቢ ሚና መጫዎት እንዳለባቸው ይገነዘባል፡፡

ዶክተር ባይሳ አክለውም ያደጉ ሀገራት ለዕድገታቸው ትልቁን ድርሻ ያበረከተው የኢኖቬሽን ና ቴክኖሎጂ መስክ በመሆኑ የዚህ ውጤት መስፋፋትና መበራከት የሀገር ዕድገት አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ global startup index 2021 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መግባታችን አበረታች ቢሆንም ካለን የሰው ሀብትና የተፈጥሮ ሀብት አንጻር ሳይንስ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ለሀገር ዕድገት እየተጫወተ ያለው ሚና በሚፈለገው መጠን አይደለም። ስለዚህ አሰራርን የሚያሻሽሉ ምቹ ፖሊስዎችን እና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎችን በመፍጠር የተቀናጀና መጠነ ሰፊ ተግባራት ማከናወን እንደሚጠበቅብን ተገልፆአል፡፡

ይህ መድረክ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ በመጠቆም ተሳታፊዎች ውጤታማና ጥሩ ተሞክሮዎችን ተለዋውጠዋል፤ የቴክኖሎጂ ሀሳባችሁንና ምርቶቻቸውን እንዲተዋወቁ፤ ትስስር እንዲፍጠሩ ብሎም የእድገት መስናክሎች እንዲፈቱ የሚያስችሉ ሐሳቦችን የቀረቡበት ነበር።በውይይት የሚኒስቴር መ/ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት የበላይ አመራሮች፣ የኢንኩቤሽን ማዕከላት እና የአክሰለረተሮች መሪዎች ስታርታፖዎች እና ኢኖቬተሮች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook