ኢትዮጵያ ሳተላይት አመጠቀች
ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ታኅሣሥ 10፣ 2012 ዓ. ም ወደ ህዋ ልካለች።
ምድርን እየቃኘች እና በፎቶ እየመዘገበች መረጃ የምትሰበስበውና “ETRSS-1” የሚል ስያሜን የተሰጣት ሳተላይት በሀገራችን የዕድገት ጉዞ ላይ ቁልፍ ሚና የሚኖራት ይህች ሳተላይት በተጓዳኝም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ ከግብርና ጋር የተያያዙ ጥናት እና ምርምሮችን ለመሥራት እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የመሠረተ ልማት ተግባራትን ለማከናወን ታስችላለች ።
Ethiopian Remote Sensing Satellite – 01 (ETRSS – 01) የተሰኘችው ሳተላይት በቻይና መንግስት የተገነባች ሲሆን በግንባታው ሂደትም በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ከቻይና አጋሮቻቸው ጎን ተሰልፈው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
ሳተላይቷ በቻይና ሀገር ውስጥ ከሚገኝ የማምጠቂያ ማዕከል ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት ወደ ህዋ የመጠቀች ሲሆን በአዲስ አበባ ውስጥም የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የተለያዩ የፌደራልና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ሳታላይቷን ወደ ህዋ የማምጠቅ ስነ ስርዓትን ከእንጦጦ ስፔስ ሳይንስ ኦብዘርቮተሪ የመከታተል ስነ ስርዓት ተከናውኗል።
በዚህ ሥነ-ሥርዓትም ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት ሳተላይት ለሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ ታሪካዊ መሰረት የምትጥል እንደሆነችና ሀገሪቱ የማይቀረውን ዓለም በተወዳዳሪነት በፍጥነት መቀላቀል እንዳለባት በማመልከት፥ ይህ የሳተላይት ጅምር ጉዞ አንድ ማሳያ መሆኑን በመናገር
“ለኛ ለኢትዮጵያውያን . . . ጨለማን እየፈራን ብርሃን የምንናፍቅ” ህዝቦች እንዳልሆንን በተግባር የተረጋገጠበት ታሪካዊ እርምጃ መሆኑ ነው” ብለዋል።
“ህዋ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው፤ ቅንጦት አይደለም” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ ናቸው።
የሳተላይቷ የመረጃ መቀበያ እንጦጦ ላይ የተሠራ ሲሆን ከማምጠቅ ሥራው ጀምሮ ቁጥጥሩ ሙሉ ለሙሉ እንጦጦ ላይ በኢትዮጵያውያን የህዋ ዘርፍ ባለሞያዎች እየተከናወነ ነው።