የዘንድሮው “5ኛው አለም አቀፍ የሰው አልባ አውሮፕላን ኮንግረንስ 2021” በቻይና ሸንዠን እየተካሄደ ነው።
ኢትዮጵያ፣ ስዊዘርላንድና ፓኪሳታን የዘንድሮ ኮንግረንስ የክብር ተጋባዥ ሀገራት ናቸው።
በቻይና የጓንዡ የኢትዮጵያ ቆንሲል ጀነራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ የሰው አልባ አውሮፕላንና የሰው ሰራሽ አስተውሎ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ቴክኖሎጂው በአቪየሽን፣ በጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ግብርና፣ አረንጓዴ ልማት፣ የመሬት አስተዳደርና የማዕድን ዘርፍ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ አምባሳደሩ በኢትዮጵያና ቻይና ተቋማት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ውስጥ የተካተተውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታዋን ለማፋጠን የድሮን ህግ ማውጣቷንና የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች በሰው አልባ አውሮፕላን ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሰማሩ አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረች ነው ብለዋል።
በቻይና አፍሪካ ጥምረት በኩል ያለው የኢትዮ ቻይና ግንኙነትም ከቻይና የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በኮንግረንሱ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ የኢንደስትሪና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የተቋም መሪዎችና ምሁራን እየተሳተፉ ነው።
የቻይናና የውጭ ሀገራት ድርጅቶ ከ200 በላይ የዘርፉን አዳዲስ ምርቶች ይዘው ቀርበዋል።