10ኛው አለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደህንነት ስብሰባ-አፍሪካ 2021 በበይነ መረብ እየተካሄደ ነው፡፡
ስብሰባው በመረጃ መረብ ደህንነትና የዲጂታል ጠላፊዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየመከረ ነው፡፡
የአፍሪካን የመረጃ መረብ ደህንነት ሁኔታ ያብራሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሃመድ (ፒ ኤች ዲ) አፍሪካ በበይነ መረብ ግንኙነት ተደራሽነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ብትሆንም በመረጃ መረብ መንታፊዎች በአመት እስከ 3.5 ቢሊየን ዶላር እንደምታጣ ተናግረዋል፡፡
ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በ469ሚሊየን ገደማ የሞባይል መጠቀሚያዎች 456.3 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ዝውውር እንደሚፈፀም ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህ እያደገ የመጣው የሞባይል የገንዘብ ዝውውር የመረጃ መረብ መንታፊዎች አይን ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ብለዋል፡፡
አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ድርጅቶች የመረጃ መረብ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዳልሆነና የፖሊሲ አውጭዎች በትኩረትና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የበይነ መረብ ግንኙነት እየጨመረ መምጣት፣ በመረጃ መረብ ደህንነት ላይ በቂ ግንዛቤ አለመኖር፣ ዝቅተኛ የዲጂታል እውቀት፣ የመረጃ መረብ ጥበቃ ባለሙያ እጥረት፣ ፍቃድ የሌላቸው ሶፍትዌሮችን መጠቀም የአፍሪካን የመረጃ መረብ ለመንታፊዎች እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካን የበይነ መረብ ደህንነት ለማስጠበቅ ከአፍሪካ 2063 አጀንዳ ጋር በተጣጣመ መልኩ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም አብራርተዋል፡፡
በሂደት ላይ ያለው የአፍሪካ የአይ ሲ ቲ አድገት ህግና ፖሊሲ፣ የኢንተርኔት መንግስት ሰነድ መዘጋጀቱ፣ የመረጃ መረብ ደህንነትና የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ (ማላቦ ኮንቬንሽን)፣ የመረጃ ደህንነት ዳሰሳ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የመረጃ መረብ ደህንነት ስብሰባ ትኩረቱን የመረጃ መረብ ደህንነት ላይ አድርጎ በየ አመቱ የሚካሄድ ስበሰባ ነው፡፡