በዲጂታል ኢኮኖሚ የሴቶችን ተጠቃሚነት ደረጃ የሚገመግምና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሴቶች ማህበር ለመመስረት የሚያስችል የበይነ መረብ ምክክር ተካሂዷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ኢትዮጵያ የሴቶችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ “አካታችነት” በሚል በትኩረት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
የሴቶች ዲጂታል ክህሎት ያለበት ሁኔታ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስጠናት እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህ ጥናት አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
አካታች የሆነ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሴቶች ዲጂታል ክህሎት ለማሳደግ እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ 3.7 ቢሊየን ሰዎች የበይነመረብ ግንኙነት ተደራሽ ያልሆኑ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
አብዛኞቹ በሴቶች የሚሸፈኑ ስራዎች ኦቶሜትድ እየሆኑ ሴቶች ከስራቸው እየተፈናቀሉ በመሆኑ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት ይገባል ተብሏል።
የአለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ባዘጋጀው በዚህ መድረክ የኢትዮጵያ የንግድ ሚኒስቴርና የኢንደስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።