ኢትዮጵያ ጠንካራ የግል መረጃ ጥበቃ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል የተባለ “የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ” ተግባራዊ ልታደርግ ነው።

አዋጁ በህገ መንግስቱ የተደነገገውን የግል መረጃ ጥበቃ ተመርኩዞ ግልሰቦች በግል መረጃቸው ላይ ያላቸውን ዝርዝር መብትና ጥበቃ የሚደነግግ ነው።

እስከ አሁን የሰዎች የግል መረጃ የማቀናበር መርሆዎች ባለመቀመጣቸውና የግል መረጃ ተቆጣጣሪ አካል ባለመሰየሙ በኢትዮጵያ ጠንካራ የግል መረጃ ጥበቃ ስርዓት ሳይዘረጋ ቆይቷል።

በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ አዋጅ በኢትዮጵያ የግል መረጃ ጥበቃ ስርዓት አለምአቀፋዊ ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ የግል መረጃ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ሀገር፣ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውሥጥ በማዘዋወር መልካም እድሎችን አሟጦ መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው የተረቀቀው።

አዋጁ የማንኛውም ግለሰብ መረጃ ሲቀናበር የግላዊ መብቱን ባከበረ መልኩ እንዲሆን የሚደነግግና ጥንቃቄ የሚፈልጉ መረጃዎችን ማቀናበርን የሚከለክል ነው።

ለህክምና አላማ ተፈልጎ በሃኪም ቤት ከተከናወነና በፍርድ ሂደት ከተወሰነ ማቀናበርን የሚፈቅደው አዋጁ በኢትዮጵያ ጠንካራ የግለሰብ መረጃ ጥበቃ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል።

ለየትኛውም አላማ የተቀናበረ የግለሰብ መረጃ አስፈላጊ ከሆነበት ጊዜ በላይ መቀመጥ እንደሌለበት የሚደነግገው አዋጁ መረጃውን የሰበሰበው የተፈቀደለት አካልም መረጃውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ለመስጠት በ3ኛ ወገን የስልጣን ክልል ውስጥ ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግ ሲያረጋግጥ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል።

ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል መረጃን ከሀገር ውጪ ለማስተላለፍ በቅድሚያ የኮሚሽኑን ፍቃድ ማግኘት ይኖርበታል።

አዋጁ የዲጂታል ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ታዕማኒ የመረጃ ልውውጥ በመፍጠር ግለሰቦች ከደህንነት ስጋት እንዲላቀቁ ያስችላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook