የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ግብዓት እየሰበሰበ ነው።
ስራ ላይ ያለው ፖሊሲ ስራ ፈጠራን ማዕከል ያላደረገ፣ የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ የመሪነት ሚና እንዲኖረው ያላስቻለና የቴክኖሎጂ ልማት ከኢኖቬሽን ጋር በሚፈለገው መልኩ ያላስተሳሰረ በመሆኑ ነው ክለሳ የተደረገበት።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) አዲሱ ፖሊሲ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽንን በመጠቀም የኢኮኖሚው ማሻሻያ ግብ የሆኑትን የስራ እድል ፈጠራ ማሳካት፣ የውጭ ገቢን ማሳደግና ሀገራዊ ብልፅግናን ማምጣትን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ረቂቅ ሰነዱ የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ የመሪነት ሚና እንዲጫወት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል። ከፌደራል ተቋማት፣ ከሙያ ማህበራትና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ ባለድርሻዎች በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት እያደረጉ ነው።
የፖሊሲ ክለሳው የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ ጥናት፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳ፣ የ10 አመት አገራዊ እና የዘርፍ ዕቅድ፣ ዘላቂ የልማት ግቦች 2030፣ የአፍሪካ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስትራቴጂ 2024 እንዲሁም አለም አቀፋዊ ልምዶችን መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ ነው።
ፖሊሲው የሚፈለገው ግብዓት ከተሰበሰበ በኋላ በሚመለከተው አካል ፀድቆ ስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል።