ከመሬት ምልከታ ሳተላይቶች መረጃ መቀበል የሚያስችል የባለ-ብዙ የሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ ተመረቆ ስራ ጀመረ።

ኢትዮጵያ ካሏት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ውጭ በሌሎች ሀገሮች ከሚተዳደሩ ሳተላይቶች መረጃዎችን ለመቀበል የሚያስችለው ይህ ጣቢያ ከ5 ሳተላይቶች መረጃዎችን መቀበል የሚችል ነው።

በቻይና፣ ብራዚል፣ እንግሊዝ፣ እና በአውሮፓ ህብረት ከሚተዳደሩ የመሬት ምለከታ ሳተላይቶ መረጃ ለመቀበል የሚያስችል የመረጃ ልውውጥ ስምምነትም ተደርሷል። ጣቢያውን መርቀው ያስጀመሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) የጣቢያው መገንባት የመረጃ አይነትና ብዛትን በማሟላት ኢትዮጵያ በህዋ ዘርፍ ያላትን ጥንካሬ ከፍ የሚያደርግ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችላትን የዲጂታል ስትራቴጂ ቀርፃ እየሰራች ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ጣቢያው በስትራቴጂው ከተካተቱ ከግብርና እሴት ማመንጨት እና ቱሪዝምን በቴክኖሎጂ መደግፍ የሚሉትን ለማስፈፀም ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አብዲሳ ይልማ ከመጀመሪያዋ ሳተላይት ብቻ መረጃ መቀበል ለኢትዮጵያ በቂ ባለመሆኑ ከሌሎች ሀገራት ሳተላይት መረጃ መቀበል በማስፈልጉ ጣቢያው መገንባቱን ተናግረዋል።

ጣቢያው የኢትዮጵያንና የጎረቤት ሀገራት የመረጃ ፍላጎትን ለማሟላትና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።

ከሳተላይት የሚወሰዱ መረጃዎች ለግብርና ስራዎች፣ ለተፈጥሮ አደጋዎች ትንበያና ቅድመ ጥንቃቄ፣ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና ለማዕድን አሰሳ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ ናቸው።

በቀጣይ ከሜትሮሎጂ ሳተላይቶች መረጃ መቀበል የሚያስችልና ከ5 በላይ ሳተላይቶች መረጃ መቀበል የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገልፁዋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook