ከፍተኛ ሃብት በማመንጨት የስራ እድል ይፈጥራሉ የተባሉ 16 የምርምር ፕሮጀክቶች ገበያውን እንዲቀላቀሉ ሊደረግ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲደግፋቸው የነበሩ የምርምር ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች ጋር ገምግሟል።

ሲደገፉ ከነበሩ 71 የምርምር ፕሮጀክቶች ውስጥ ዝቅተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡት ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በማቋረጥ በተግባር የተረጋገጡ 16ቱን ወደ ንግድ እንዲቀየሩ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሰራ አስታውቋል።

የምርምር ፕሮጀክቶቹ በግብርና፣ በቆዳ፣ በኢነርጂ፣ በጤና፣ በኮንስትራክሽን፣ በአይሲቲና በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰሩ ናቸው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) በምርምር ዘርፍ የተሰማሩትንና በኢንደስትሪው መካከል ያለውን ክፍተት በመሙላት ሁለቱ በቅርርብ እንዲሰሩ ማድረግ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመፍታትም ከተመራማሪዎች የሚመጡ የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ማድረግ፣ በመንግስትና በግለሰቦች የሚሰጡ የተናጠል የምርምር ድጋፎችን ወደ አንድ ማዕከል ማምጣት እና ሃሳብ ያላቸውን የፈጠራ ባለሙያዎች ገንዘብ ካላቸው ሰዎች ጋር የሚያገናኝ የዲጂታል አሰራር መዘረጋት ላይ መንግስት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

እነዚህ ሃብት በማመንጨት የስራ እድል ይፈጥራሉ የተባሉና ወደ ንግድ እንዲገቡ የተመረጡ የምርምር ፕሮጀክቶችን ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ለህዝብ የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል ተብሏል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook