ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል በድጋሜ አረጋገጠ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ዳይሬክተር ሚስተር ኦስማን ዲዮን ከተመራ ከፍተኛ ልዑካን ጋር ተወያይተዋል።

ዓለም ባንክ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የልማት ስራ በመደገፍ እና ከሃገር በቀል ኢኮኖሚክ ሪፎርም አጀንዳ የተቀዳውን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጅ ለመተግበር የሚያስችል ፕሮጀክትን እያገዘ ነው ያሉት ሚኒስትሩ እስከዛሬ ለነበረው ትብብር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት አስቻይ የሆኑት ማለትም የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፋት፣ የዲጂታል መንግስት ትግበራ፣ የዲጂታል እውቀት፣ የሪጉላቶሪ አቅም ግንባታ፣ የዲጂታል ግብይት፣ የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሌሎች መንግስታዊና የግል ሴክተር ባለ ድርሻ ጋር የሚያከናውናቸውን ተግባራት የዓለም ባንክ በመደገፍ ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ አያይዘው ገልጸዋል።

የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኡስማን ዲዮንም በበኩላቸው የዲጂታል ስትራቴጂውንና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ዕቅዶች በትብብር መፈጸም የሚያስችሉ ተግባራትን ለመደገፍ ዓለም ባንክ ሁሌም በራቸው ክፍት እንደሆነ ገልጸው በተለይም ስራ ለመፍጠር፣ ቀጠናዊ ትብብርን ለማሳደግ፣ የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን፣ የግሉን ሴክተር ለማሳተፍና በሁሉም ዘርፎች አካታችነትን ለማምጣት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ወሳኝ በመሆኑ ከመቸውም በላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

የዓለም ባንክ ከፍተኛ አመራሮችና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በቴክኒካዊና አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ በጥልቀት ከተወያዩ በኋላ በሁለቱም ተቋሞች በኩል የጋራ መግባባት የተደረሰባቸውንና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በመለየት ባጠረ ጊዜ ውስጥ ወደ መፈጸም እንደሚገቡ ተስማምተዋል። በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ዳይሬክተር ሚስተር ኦስማን ዲዮን የተመራውን ቡድን ለነበራቸው ፍሬያማ ውይይት አመስግነው ቀጣይ ትግበራወች ውጤታማ እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook