ዜጎች በዲጂታል መታወቂያ ላይ እንዲተማመኑ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ ነው።

በኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ግብዓት ለማሰባሰብ የሚያስችል ምክክር ተደርጓል። ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ ዜጎች ወጥ የሆነ መለያ ኖሯቸው በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቀልጣፋና ታዕማኒ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

ጠንካራ፣ አስተማማኝ፣ ተደራሽ እና ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ መለያ ስርዓትን በመዘርጋት ከወንጀል ጋር የተያያዙ ስጋቶችን በመቀነስ ሀገራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥም ያስችላል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለሚደረግ ሽግግር ዲጂታል መታወቂያ አንዱ አስቻይ ሁኔታ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች በዲጂታል መታወቂያ ላይ እንዲተማመኑ ለማድረግ የህግ እና የቁጥጥር ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህንን መተማመን ለመፍጠር የዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

የብሄራዊ መታወቂያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል ዲጂታል መታወቂያ ድግግሞሽን በማስቀረት የሃብት ብክነትን በመቀነስ በነዋሪዎች መካከል ፍትሀዊነትን ለማስፈን እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ተጨማሪ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ ከፌደራልና ከክልል መንግስት የስራ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook