የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን የመረጃ ደህንነት የሚያስጠብቅ “የኤሌክትሮኒክ መንግስት የኢንፎርሜሽን ደህንነት ፖሊሲ” እየተዘጋጀ ነው፡፡

ፖሊሲው የመንግስት አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ለዜጎች ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመረጃ መረብ ደህንነትን ለማስጠበቅና በሁሉም ተቋማት ወጥነት ባለው መልኩ ለመተግበር የሚያስችል ነው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለረቂቅ ፖሊሲው ተጨማሪ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ ከፌደራል ተቋማት፣ ከክልልና ከግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የመረጃ መረብ ደህንነት ሥራ አመራር በአግባቡ ካልተመራ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶችን ስለሚያስከትል ፖሊሲው ይህንን ችግር ለመቅረፍና ወጥ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል፡፡

በዓለማችን በተቋማት ላይ በሚፈጸም ጥቃት በደቂቃ 2.9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይታጣል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ፖሊሲው ኢትዮጵያ ለዚህ የሚመጥን ዝግጅት ለማድረግ እንደሚርዳት ተናግረዋል።

ፖሊሲው በመንግስት መስሪያ ቤቶች በኩል ለዜጎች፣ ለሠራተኞች፣ ለንግድና ለሌሎች መንግስታዊ ተቋማት የሚዘረጉ መሰረተ ልማቶችና የሚለሙ አገልግሎቶች በመረጃ መረብ ደህንነት ሥራ አመራር ደረጃ ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook