ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የመጀመሪያው ብሔራዊ የበይነመረብ አስተዳደር ጉባኤ በአካል እና በኦንላይን ጥምረት ተካሄደ።
ጉባኤው በመጪው ዓመት ህዳር ወር በአዲስአበባ የሚካሄደው የ 17ኛው ዓለምአቀፍ የበይነመረብ አስተዳደር ጉባኤ(ፎረም) አካል ነው።
በጉባኤው የበይነመረብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች፣ ተመጣጣኝ እና ትርጉም ያለው የበይነመረብ ተደራሽነት፣ የበይነመረብ ተደራሽነት እንደ መሰረታዊ መብት በሚሉት ጉዳዮች ላይ በትኩረት ተመክሮባቸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ከበይነ መረብ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አሉታዊ ጫናዎችን ለመቋቋምና ዜጎች በበይነ መረብ የሚያደርጉት ግኑኝነት አስተማማኝ እንዲሆን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ አዋጆች በስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን ተናግረዋል።
በቀጣይ ዓመት የሚካሄደው 17ኛውን ዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ስኬታማ ለማድረግ፣ የሚነሱ ውይይቶች ሁሉን አቀፍ፣ ከ ዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የተናበቡና የሚነሱ ሃሳቦች በነጻነት የሚንሸራሸሩበት መድረክ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር) በይነ-መረብ ከጥቅሙ ባሻገር ከመረጃ መረብ ወንጀሎች፣ ከጥላቻ ንግግሮች፣ የሀሰትና የተዛቡ ዜናዎች ስርጭት አኳያ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት ተናግረዋል።
ጉባኤው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚነሸራሸሩበት መሆኑን ጠቁመዋል። ጉባኤው ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት ለምታስተናግደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ ምረብ አስተዳደር ጉባኤ መሰረት የሚጥል ነው ተብሏል።
የቀጣዩ ዓመት ጉባኤ የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባት፣ ኢትዮጵያ በመስኩ እየሰራች ያለውን ስራ ለዓለም ለማሳየት፣ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ተሰሚነት ለማሳደግ፣ ከተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
የበይነ-መረብ አስተዳደር ፎረም አስገዳጅ የሆኑ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት ሳይሆን ውሳኔ አመንጪና ሰጪ የሆኑት የግሉ ዘርፍና መንግስት በጉዳዮቹ ላይ መክረው የመረጃና የፖሊሲ ሀሳብ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡