የሚኒስትሮች ምክር ቤት ብሄራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ፀድቆ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ ለመሆኑ የዲጂታል ክፍያ ምን ማለት ነው? የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂስ ምን ምን ጉዳዮችን አካትቷል?

ቀጣዩ ፅሁፍ የተወሰነ ማብራሪያ አካትቷል፡፡

የዲጂታል ክፍያ ብያኔ፡-

ዲጅታል ክፍያ ማለት ከጥሬ ገንዘብ ልውውጥ በመውጣት በክፍያ ካርድ፤ ኤልክትሮኒክ ገንዘብ፤ ገንዘብ በራሳቸው በሚከፍሉ ማሽኖች (ኤ ቲ ኤም)፣ ገንዘብ በሚያስተላልፉ ማሽኖች፣ በሞባይል ስልክ እና በመሳሰሉት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ገንዘብን ማስተላለፍ እና ክፍያ መፈፀም ማለት ነው፡፡

ብሄራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ፡-

ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይት በሁለትና ሶስት እጥፍ እያደገ መጥቷል፡፡ በተለይ የሞባይል ግብይት ከ200 በመቶ በላይ እድገት አሳይቷል፡፡ ይህ የዲጂታል ክፍያ አካታችና በሃላፊነት ስሜት የሚመራ ስነ ምህዳር እንዲኖረው የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል፡፡

ስትራቴጂው የተዘጋጀው አካታችና በኃላፊነት ስሜት የሚተገበር የዲጂታል ክፍያ ስነምህዳር መገንባት ለኢትዮጵያ ህዝብና ኢኮኖሚ እጅግ በጣም አስፈላጊ እና አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ታስቦ ነው፡፡

የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን መተግበር ግልጽነትና ውጤታማነትን ከማስፈን፣ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር፣ የፋይናንስ አካታችነትና ሁሉን አቀፍ እድገት ከማምጣት አኳያ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ በጥሬ ገንዘብ መጠቀምን በመተው ወደ ዲጂታል አማራጭ መሄድ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ያግዛል፣ የህዝቦችን  የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል አጋጣሚዎችንም ይፈጥራል፡፡

የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ሰነዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያ ስነ-ምህዳሩን በማዘመን ውስን የጥሬ ገንዘብ  እንቅስቃሴ ያለውና የፋይናንስ አካታችነቱ የጎለበተ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ፍኖተ ካርታ በመሆን ያገለግላል፡፡

የብሔራዊ ዲጅታል ክፍያ ማዕቀፍ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ማዕቀፍ ራዕይ፣ ራዕዩን ለማሳካት የሚያግዙ ስትራቴጂክ ምሰሶዎችና እንደ መደላድል የሚያገለግሉ ቁልፍ አስቻይ ሁኔታዎችን ያካተተ ነው፡፡

የብሔራዊ ዲጅታል ክፍያ ስትራቴጂ ራዕዩ

የብሔራዊ ዲጅታል ክፍያ ስትራቴጂ ራዕዩ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተወዳዳሪ፣ ወጭ ቆጣቢ፣ በፈጠራ የታገዘና ሃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ የክፍያ ከባቢያዊ ሁኔታ በመገንባት ውስን ጥሬ ገንዘብን የሚጠቀምና የፋይናንስ አካታችነትን የተላበሰ ኢኮኖሚ እንዲኖር ማገዝ ነዉ፡፡

ስትራቴጂው የቆመባቸው ምሰሶዎች፡-

ይህ ብሔራዊ ዲጅታል ክፍያ ስትራቴጂ አራት ዋና ዋና ምሰሶዎችን ታሳቢ አድርጓል፡-

1ኛ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አካታችና ተናባቢ መሰረተ ልማት መገንባት፣

2ኛ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትን  መተግበር፣

3ኛ ወጥነት ያለውና ሁሉን አቀፍ (ውጤታማ)  የህግ ድንጋጌዎችና የክትትልና ቁጥጥር ማእቀፍ ማዘጋጀት፣

4ኛ ለአዳዲስ ግኝቶችና ፈጠራዎች አስቻይ ከባቢን መፍጠር ናቸው፡፡

የስትራቴጂው አስቻይ ሁኔታዎች፡-

ከኢትዮጵያ መንግስት ሁሉን አቀፍ የሪፎርም አጀንዳ ጋር እንዲጣጣም ሆኖ የተዘጋጀው ስትራቴጂው ለዋና ዋና ምሰሶዎቹ መደላድልን ለመፍጠር የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎች ተለይተውለታል፡፡

1ኛ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ አገርአቀፍ የክፍያ ስርዓትን ለመገንባት ያለው ቁርጠኝነት፣

2ኛ በዲጂታል ክፍያ ከባቢያዊ ሁኔታ ላይ የአቅም ግንባታ ስራዎች ለማከናወን ቅድሚያ ትኩረት መሰጠቱና አስፈላጊውን ሃብት መመደቡ፣

3ኛ ከአገሪቱ የልማት እድገት ሪፎርም ስራዎችና ፖሊሲዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ቅንጅትና መናበብ እንዲኖር መደረጉ፤ እንዲሁም፣

 4ኛ ውጤታማ የአስተዳደርና የትግበራ እቅድ ግንባታና ቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያዎችን በማዘጋጀት አፈጻጸምን መለካት የሚያግዝ አሰራር መኖሩ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን የበይነ መረብ ጥቃቶችና ዲጂታል ማጭበርበር ቢኖሩም ዲጂታል ክፍያ ከጥሬ ገንዘብ ዝውውር በተሻለ ደህንነቱ የተጠበቀ የክፍያ አማራጭ ነው፡፡ የዲጂታል ማጭበርብሩና የበይነ መረብ ጥቃቱም ቢሆን ጠንካራ የበይነ መረብ ጥበቃ ስርዓት በመዘርጋት መከላከል ይቻላል፡፡

ከጥሬ ገንዘብ ወደ ዲጂታል ክፍያ የሚደረግ ሽግግር በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የረጅም ጊዜ የወጭ ቅነሳ ጥቅምን ያስገኛል፡፡ በግለሰብና ተቋማት መካከል ደግሞ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ጊዜን፣ ጉልበትንና ወጪን በመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

ሰዎች ከጥሬ ገንዘብ ጋር ባላቸው ቁርኝት ከዚህ ስርዓት ውስጥ በፍጥነት ለመውጣት የሚቸገሩ ቢሆንም የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ ወደ ስርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ ላይ መንግስት እና ወኪሎች ሊሰሩ ይገባል፡፡

የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ የፋይናንስ አካታችነትን የሚያረጋግጥ እድገት ከማምጣት አኳያ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

1ኛ ቀልጣፋና ወጭ ቆጣቢ መሆኑ፡- ጊዜን፣ ወጪንና ጉልበትን መቆጠቡ

2ኛ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ግልጽነት የተሞላበት መሆኑ፡- ከጥሬ ገንዘብ ዝውውር ይልቅ ደህንነቱ የተጠበና ግልፅነት የተሞላበት መሆኑ

3ኛ የፋይናንስ አካታችነቱ፡- ሁሉን የህብረተሰብ ክፍሎች ማካተቱ

4ኛ፡- የሴቶች የኢኮኖሚ ተሳትፎ ማሳደጉ፡- የዲጂታል ክፍያዎችን መተግበር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ በተለያዩ ሀገራት ባለው የባህል ጫና ምክንያት ሴቶች የኢኮኖሚ ነፃነታቸው የተገደበ በመሆኑ ምክያት ይህ የክፍያ ስርዓት ለሴቶች ነፃነትን በመስጠት ትልቅ አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡

ስትራቴጂውን ለመተግበር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች

በኢትዮጵያ ዲጂታል ክፍያን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር የመሠረተ ልማት፣ የመተግበር፣ የህግ ማዕቀፍ እና የፈጠራ ችግሮች እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍም መንግስት የህግ ማዕቀፍ ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook