የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር “ብሄራዊ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት” ሊዘረጋ ነው።

ስርዓቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የስራ ፍላጎትና ቅጥር የሚሰንድ፣ ስራ ፈላጊና ቀጣሪን በቀላሉ የሚያገናኝና አጠቃላይ የስራ ገበያን የሚያስተዳድር ዲጂታል ስርዓት ነው።

ስራ ላይ የተሰማራ ህዝብ፣ ስራ የሚፈልግ የሰው ሃይል ብዛት እና ገበያው የሚፈልገው የሰው ሃይልን የሚመለከቱ መረጃዎችን ወደ ስርዓቱ በማስገባት ቀላል የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ያስችላል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያስመርቋቸው ተማሪዎች፣ ተማሪዎቹ የተመረቁበት የሙያ ዘርፍ፣ የመንግስት ተቋማትና የግል ድርጅቶች ለቅጥር የሚፈልጉትን የሰው ሃይልና የሙያ ዘርፍ ሰብስቦ ለመያዝም ያግዛል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ፒ ኤች ዲ) የስራ ፍላጎትና አቅርቦት የተሳለጠና የዘመነ እንዲሆን ብሄራዊ የስራ ገበያ ስርዓቱ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል። ወቅታዊ የስራ መረጃ ለዜጎች እንዲደርስ ለማድረግ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) ሀገራዊ የመረጃ ስርዓት እንዲዘርጋ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የህግ ማዕቀፎችንና መሰረተ ለማትን በመዘረጋት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር የሚዘረጋው ብሄራዊ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓቱ የተቋማትን መናበብና በጋራ መስራት ስለሚጠይቅ ሁሉም ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የአለም አቀፉ የስራ ድርጅት ተወካይ አይዳ አወል ስርዓቱ የተደራጀ መረጃን በመተንትን ለፖሊሲ አውጪዎች ትልቅ ግብዓት ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ስርዓቱን ለመዘርጋት በሚያደርገው ጥረትም የአለም አቀፉ የስራ ድርጅት እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

እስከ ዛሬ ስራን የተመለከቱና በወረቀት የተሰነዱ መረጃዎች ወደ ስርዓቱ እንዲገቡ የሚደረግ ሲሆን የስራ ገበያ መረጃን አጠቃልሎ በመያዝ የተለያዩ ጥናቶችን በቀላሉ ለማድረግ ያስችላል።

ስርዓቱ በሀገሪቱ በየሙያ ዘርፉ ያለ አጠቃላይ የሰራተኛ ብዛት፣ ስራ ላይ የተሰማራ የሰው ሃይል፣ ስራ ፍለጋ ላይ ያለ ሰው ብዛትን አጠቃልሎ የሚይዝ ነው።

ስራውን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአለም የስራ ድርጅት እና ጂ አይ ዜድ በትብብር ይከውኑታል።

ብሄራዊ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ግንባታና ትግበራን በጋራ ለመስራት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የቃል ኪዳን ፊርማ ስነ-ስርዓት አድርገዋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook