የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ማዕከል ፕሮጀክት ግንባታ 84 በመቶ ደረሰ

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየተገነባ ያለውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት/Innovation and Technology Talent Development Institute/ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፌደራልና የክልል ቢሮ አመራሮች ጎብኝተውታል።

አመራሮቹ የአረንጓዴ አሻራቸውን በማዕከሉ ቅጥር ግቢም አኑረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ ፕሮጀክቱ ባለፉ ዓመታት በነበሩ አገራዊ ችግሮች ምክንያቶች መዘግየት አጋጥሞት እንደነበር ገልፀው በ2013 ሁለተኛ ሩብ ዓመት መጀመሪያ ወራት ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ ስራ ሲጀምር ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር በአገራችን የሚገኙ ባለተሰጥኦዎችን አሰባስቦ ተሰጥኦዋቸውን በማጎልበት ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩበት ስለሆነ መላ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉትና እንዲሳተፉበት ጥሪ አቅርበዋል።

ለስልጠናና ትምህርት እንዲሁም ተሰጥኦ ማፍለቅና ትግበራ የሚውሉ የቁሳቁስ እገዛና ድጋፍ ከልዩ ልዩ አካላት መገኘት ጀምሯል፡፡

ተቋሙ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካና ዘላቂነት እንዲኖረው የአሠራር መመሪያዎችን፣ የትብብር ማዕቀፎችን፣ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትን፣ የተውህቦና የክህሎት መለያ መስፈርቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ቀድሞ የማዘጋጀት ስራ ከወዲሁ እየተሰራ ነው፡፡

የግንባታ ስራ ተቋራጩ ስራ አስኪያጅ ኢንጂኔር መስፍን ባልቻ የቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ፣ ወርክሾፖች፣ የመማሪያ ክፍል እና የማደሪያ ሕንጻዎችን በልዩ ትኩረት ተገንብተው ከ78% – 90% የአፈጻጸም ደረጃዎች ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው ያለበት አማካይ የአፈጻጸም ደረጃ ከ84 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡

ግንባታው ከሦስት ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በተሰጠ አምስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በተያዘ የመንግስት በጀት የተጀመረ ነው።

ከመላው ኢትዮጵያ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል እስከ 1000 ባለተሰጥኦዎችን መልምሎና ተቀብሎ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለግን ተሰጥኦዋቸውን በማልማት፣ በማጎልበትና ወደ ተጨባጭ አምራችነት በመቀየር ለአገራዊ ብልጽግና መሠረት ለመጣል ታስቦ እየተገነባ ያለ ተቋም ነው፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook