የአውሮፓ ሀገራት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የሚሰሯቸው ስራዎች አፍሪካውያንን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች፡፡

የአፍሪካ- አውሮፓ የሳይንስና ኢኖቬሽን ስብሰባ በበይነ መረብ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ እየተሳተፉ ያሉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) የአውሮፓ ሀገራት በሳይንስ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰሯቸው ስራዎች አፍሪካዊያንን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዘርፉ የሚወጡ ህግና ፖሊሲዎች አፍሪካውያንን እና የአፍሪካ ጉዳዮችን ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትብብር በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመጠገን አቅም ይፈጥራል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በቀጣይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎችንም ለመድረኩ አብራርተዋል፡፡

የአፍሪካ- አውሮፓ የሳይንስና ኢኖቬሽን ስብሰባ በአውሮፓና በአፍሪካ መካከል ያለውን የሳይንስና ኢኖቬሽን ግንኙነት በማጠናከር ለዘርፉ ተዋናዮች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ የሚካሄድ ስብሰባ ነው፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook