መተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሠረተው የኢትዮ-ሩስያ ወዳጀነት በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በክብር እንግድነት በተገኙበት በአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ ግቢ ውስጥ የተከበረውን የሩሲያ ቀን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀው ታሪካዊ ግኑኙነትና ጠንካራ ወዳጅነት አሁንም በዘርፈ ብዙ ትብብሮች ታጅቦ ቀጥሏል በማለት ገልፀዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለው የሩሲያ ህዝብና መንግስት በትምህርት፣ በዕዳ ስረዛ እና በተለይም በአስቸጋሪ ጊዜ በተባበሩት መንግስታት በፀጥታው ምክርቤት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላደረገችው ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ይቭጌኒ ተርኪን በበኩላቸው የኢትዮጵያና ሩሲያ ታሪካዊ ግኑኙነት ተጠናክሮ ወደ ላቀ ትብብር እንዲሸጋገር የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ገልፀው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለሩሲያ መንግስትና ሕዝብ ላሳዩት አጋርነትና ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡