የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የሚመራው የንግድ ስራ ቅልጥፍና ማሻሻያ ስራ ያለበትን ደረጃ የሚመለከት ሪፖርት ቀርቦ ብሄራዊ ኮሚቴው ተወያይቶበታል።
የስራ ቅልጥፍና ፕሮግራም የንግድ ሥርዓቱን ለማሻሻል፣ የግል ዘርፉን እድገት ማነቆዎች ለመፍታትና የሪፎርሙን ውጤቶች ለመለካት የተነደፈ ነው፡፡
የማሻሻያ ፕሮግራሙ ተቋማት፣ አገልግሎት ፈላጊዎች፣ ነጋዴዎችና አልሚዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡና እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው። ኢትዮጵያ የስራ ቅልጥፍና መለኪያ ከሆኑት 10 መስፈርቶች ውስጥ 7ቱ ላይ ማሻሻያ ማድረጓ በሪፖርቱ ተገልጧል።

የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ አዳዲስ ስራዎች እንዲፈጠሩና ኢኮኖሚው እንዲያድግ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት አለበት ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) የተቋማት ከፍተኛ አመራሮች መቀያየር፣ ተቋማት ለሚወጡ ህጎች የሚመለከታቸውን የአስተያየት ምላሽ አለመስጠት፣ የባንኮች ወደ አንድ ክፍያ ስርዓት አለመምጣት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ባለፈው አመት በወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ በንግድ ስራ ቅልጥፍና ከዓለም ሀገራት 159ኛ ደረጃ ላይ ስትሆን በሚቀጥሉት አመታት ይህንን ደረጃ 100ዎቹ ዝርዝር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ነው።
በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጠራር አባይን ጨምሮ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።