የኢትዮጵያ መንግስትና የ6 ከተሞች ፖርታሎች ተመርቀው ስራ ጀመሩ።

ፖርታሎቹ የኢትዮጵያ መንግስትና ከተሞችን የሚመለከቱ መረጃዎች ሁሉ ተሰንደው ለህዝብ ተደራሽ የሚደረጉበት ሲሆን የየከተሞቹ ከንቲባዎችና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀው ስራ ጀምረዋል።

ፖርታሎቹ ዜጎች አገልግሎት የሚያገኙበትና የሚጠይቁበት፣ የተሟላ መረጃ የሚያገኙበት፣ የውጭ ጎብኚዎች ስለ ከተሞቹና ስለ ኢትዮጵያ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) መራራቅ ፈጥሮት የነበረውን ችግር ያስወገደ ዓለም ውስጥ እንደመሆናችን በራችንን ለዓለም ክፍት ለማድረግ ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ የከተሞች ፖርታል ልማት አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፖርታሎቹ ዜጎች ባሉበት ሆነው ቀልጣፋ አግልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የከተማ ፖርታሎቹ ሳይቆራረጡ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡና በወቅታዊ መረጃዎች የተሞሉ እንዲሆኑ የየከተማዎቹ ኃላፊዎች በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት የኢትዮጵያ መንግስት ፖርታል፣ የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ አዳማ እና አርባምንጭ ከተሞች ፖርታሎች ናቸው።

ለየከተሞቹ ባለሙያዎች ፖርታሉን እንዲያስተዳድሩ፣ መረጃ እንዲያከማቹ፣ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እንዲጨምሩ፣ አጠቃቀሙን እንዲያውቁ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስልጠና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰጥቷል።

የከተሞቹ ከንቲባዎችና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊዎች ፖርታሎቹ ሳይቆራረጡ አገልገሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል የቃል ኪዳን ሰነድም ፈርመዋል።

ሚኒስቴሩ በቀጣይ በሌሎችም ከተሞች ፖርታሎችን የማልማት እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook