የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማስተርካርድ የመንግስት አገልግሎት የክፍያ ስርዓትን ለማዘመን የሚያስችላቸውን ሰምምነት አድርገዋል፡፡
ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግስት የማስተርካርድ የክፍያ አማራጭን ከኢ ሰርቪስ አገልግሎት ፖርታል ጋር በማቀናጀት ዜጎች ክፍያዎችን ኦንላይን እንዲፈፀሙ ያስችላቸዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) ጥረታችን ኢትዮጵያን ከጥሬ ገንዘብ ህትመትና ስርጭት ወጪ ማላቀቅና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂያችን ተግባራዊ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ከማስተር ካርድ ጋር የሚደረገው ትብብር ሁለገብ ዲጂታል የክፍያ መፍትሄዎችን በማቅረብ ዜጎች በማንኛውም የባንክ ካርድ ክፍያ እንዲፈፀሙ ያስችላቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የገቢ አሰባሰብን ለማሻሻል እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካ ስራ አስኪያጅ ሸርያር አሊ ቀልጣፋ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ፈጠራ የታከለበት የዲጂታል የክፍያ አማራጮችን በመዘርጋት የኢትዮጰያ መንግስትን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ በሚቀጥለው ሳምንት የሚጀመር ሲሆን ዜጎች ከውጭ ሀገራት ጭምር ባሉበት ቦታ ሆነው ለተጠቀሙት የመንግስት አገልግሎት በማሰተር ካርድ የክፍያ አማራጭ ክፍያዎችን ኦንላይን መክፈል ይችላሉ፡፡
በመጀመሪያው ዙር የትግበራ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅት አባላት ይህንን የክፍያ መተግበሪያ አማራጭ በመጠቀም ፍቃድ ለማውጣትና ለማደስ በማንኛውም የክፍያ ካርድ አይነት ክፍያ መፈፀም ይጀምራሉ፡፡
ይህንን አሰራር ለመተግበር ማስተር ካርድ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስምምነት ላይ የደረሱት በ2020 ሲሆን ይህም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቲጂን” መሰረት በማድረግ ነው።