የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በመንግስት፣ በግሉ ዘርፍ እና በዜጎች ትብብር ትግባራዊ የሚደረግ ነው።

በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ ዲጂታይዜሽን፣ ዲጂታላይዜሽን እና ዲጂታል የሚባሉ 3 ፅንሰ ሃሳቦች አሉ። ፅንሰ ሃሳቦቹ ከተለምዷዊው የወረቀትና የአካል ምልልስ ያለበት አሰራር ወይንም ማንዋል በመውጣት ወደ ዲጂታል አሰራር ለመግባት በሚደረገው ሽግግር ውስጥ የሚተገበሩ ናቸው።

ከተለምዷዊው አሰራር ሽግግር በማድረግ ሂደት ውስጥ ቅድሚያ የሚገኘው ዲጂታይዜሽን የሚባለው ፅንሰ ሃሳብ ነው። ዲጂታይዜሽን ማንዋል አሰራሮችን፣ የፅሁፍ መዛግብቶችን፣ የመረጃ ልውውጥና ሂደትን በኤሌክትሮኒክስ መሳሪዎች በአንድ የመረጃ ቋት ውስጥ የማሰቀመጥ አሰራር ነው። ለምሳሌ በወረቀት ተመዝገበው የተቀመጡ የዜጎች መረጃዎች፣ የተሸከርካሪ ምዝገባን የያዙ የወረቀት መረጃዎች፣ በስራ ውስጥ በወረቀት የተመዘገቡ መረጃዎች ሁሉ በኤሌክትሮኒክ የመረጃ ቋት በሁሉም ቦታ ወቅታዊ ሆነው  ማግኘት ሲቻል ዲጂታየዜሽን ይባላል።

ከዲጂታይዜሽን ሂደት ቀጥሎ የሚገኘው ደግሞ ዲጂታላይዜሽን ነው። ዲጂታላይዜሽን በነበረው ቴክኖሎጂ ላይ አዳዲስ አሰራሮችን እና እሴት ጨምሮ ስራዎችን አውቶሜትድ ማድረግ ሲቻል ነው። ለምሳሌ ዜጎች መንጃ ፍቃድ፣ የመድህን አገልግሎት አና የተሸከርካሪ ምዝገባን በአንድ አድራሻ (ፖርታል) ማግኘት ሲችሉ  ዲጂታላይዜሽን እየተተገበረ ነው ይባላል።

መጨረሻ ረድፍ ላይ የሚገኘው የዲጂታል መዋቅራዊ ለውጥ (ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን) ነው። ዲጂታል መዋቅራዊ ለውጥ ዲጂታላይዝድ የሆኑ የአሰራር ሂደቶችን በማቀናጀት አገር አቀፍ አውቶሜሽን ማሳካት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የአሰራር ሂደቶችን የበለጠ በማዘመን እና መሰረተ ልማቶችን በማሻሻል ከዚህ ቀደም ያልታዩና ያልታሰቡ ውጤቶችን ማግኘት ማለት ነው። የመንግስት አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል መልኩ ይሰጣሉ። ንግዶች በዲጂታል መልክ የተገበራሉ። አዳዲስ እና ዘመኑ ያፈራቸው ዲጂታል አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ።  ለምሳሌ የሰው ሰራሽ አስተውህሎን በመጠቀም በሰው አልባ ተሸከርካሪ ዜጎችን በተቀላጠፈ መልኩ ማጓጓዝ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ምግብና መድሃኒት ማመላስ በዲጂታል ስርዓት ውስጥ የሚተገበሩ ናቸው።

ዲጂታል መዋቅራዊ ለውጥ በመንግስት፣ በግሉ ዘርፍ እና በዜጎች ትብብር ትግባራዊ የሚደረግ ነው። መንግስት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን እና መሰረተ ልማት ማሟላትን የመሳሰሉ አስቻይ ስርዓቶችን ይዘረጋል። የግሉ ዘርፍ ደግሞ በዲጂታል አሰራር ውስጥ የመሪነት ሚና ይጫወታል። ለማህበረሰቡ የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በዲጂታል መልኩ እንዲሆኑ ለማድረግ ስርዓት እና አሰራር በመዘርጋት ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። ዲጂታል አሰራር ተዘርግቶ ካለተጠቃሚ ዋጋ ስለሌለው ማህበረሰቡ ደግሞ የዲጂታል አሰራሮችን በመጠቀም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን ለማሳካት የራሱን አስተዋፀኦ ያደርጋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook