ፎረሙ በሳይንቲፊክ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያና ፓኪስታን ያላቸውን ልምድ እንዲለዋወጡና በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) በኢትዮጵያ ከፓኪስታን አምባሳደር ሚስተር ሾዛብ አባስ ጋር የኢትዮ-ፓኪስታን ሳይንትፊክ ዲፕሎማሲ ፎረም ምስረታና ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) ፎረሙ እንዲመሰረት ከዚህ ቀደም የተደረጉ ስምምነቶችን በማጠናከር ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።
የሳይንቲፊክ ፎረሙ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ይረዳል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለፎረሙ ስኬት ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ትወጣለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሚ/ር ሾዛብ አባስ የሳይንትፊክ ፎረሙ በአይቲ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በውሃ ቴክኖሎጂ፣ በጤና እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ምርምር የሚያደርግና የዕውቀት ሽግግር የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የሳይንትፊክ ፎረሙ እንዲመሰረት የሚያስችሉ የትብብር ማዕቀፎችና ካሁን ቀደም ስምምነት ተደርሶባቸው የቆዩ የመግባቢያ ሰነዶች ፀድቀው በቅርቡ ወደ ስራ ለመግባት ተስማምተዋል።
ፓኪስታን “የኢትዮ-ፓኪስታን ሳይንትፊክ ዲፕሎማሲ ፎረም” እንዲመሰረት ጥያቄ ባቀረበችው መሰረት ነው ከስምምነት የተደረሰው።