የኢኖሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን የማገዝ ተልዕኮውን እንዲወጣ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ ነው!!!

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዘርፉን የ2014 በጀት ዓመት እቅድና የ2015 በጀት ዓመት አቅድ አፈጻጸም የተመለከተ ምክክር ከክልል የዘርፉ ቢሮ ኃላፊዎችና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች ጋር በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እያደረገ ነው።

የምክክር መድረኩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒኤችዲ) በንግግር ከፍተውታል። እንደ ዶክተር በለጠ ሞላ የምክክር መድረኩ ኢትዮጵያ አገራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲን በመከለስ በማጽደቅ ወደ ስራ በገባችበት ወቅት የሚከናወን በመሆኑ አገራዊ አቅም የሚፈጥር ወሳኝ መድረክ ነው ብለውታል።

አገራችን በበርካታ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ላይ ብትሆንም የፌደራል መንግስትና ክልሎች በጣምራ፣ በመተሳሰብና በመቀራረብ ከሰሩ ችግሮችን መሻገር ይቻላል።

ችግሮችን መሻገር የምንችለው ግን እውቀት መር የአሰራር ስርዓት ስናሰፍን ነው ያሉት ክቡር ሚኒስቴሩ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ደግሞ እውቀት መር የችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ዓይነተኛ አቅም ነው ብለዋል።

በ2014 በጀት ዓመት እንደ አገር ለዘርፉ ትግበራ አስቻይ ሁኔታዎች ለማንበር ተሰርተዋል።

በተለይም ለክልሎችም ጭምር አቅም የሚሆኑ የፖሊሲ፣ የሕግ ማዕቀፍና እና ለ2015 እቅድ መነሻ የሚሆኑ ዐበይት ስራዎች ተከናውነዋል ሲሉ ገልጸዋል። ዶክተር በለጠ በንግግራቸው የየአገራት የትናንት የእድገት ምንጭ የተፈጥሮ ሃብት ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል።

የዛሬው ዘመን የእድገት ሚስጥር የሚቀዳው ግን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ መሆኑ ተረጋግጦ ያደረ ሐቅ ነው ብለዋል።

እንደ ኢትዮጵያ የተቀመጠው አገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ውጤታማ እንዲሆንና ዘርፉ የሚጠበቅበትን የኢኮኖሚ አመንጭነትና የአስቻይነት ጣምራ ሚናውን እንዲወጣ በሁሉም ክልሎች መንግስታት ዘንድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል። በዘርፉ እንደ አገር የተሰጠውን ትኩረት ያክል በሁሉም ክልሎች ስላልተሰጠው ሁሉም አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት አስፈላጊውን ድጋፍ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ያደርጋል።

በተጨማሪም የአደረጃጀት የስያሜ፣ የሰው ኃይል ችግር ያለባቸውን በመለየት ለማስተካከል፣ ለማገዝና ለማጠናከር ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር እንሰራለን ብለዋል። መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የዋናው መስሪያቤት፣ የተጠሪ ተቋማትና የየክልሎች አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ይኾናል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook