በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከሌሎች የልማት አጋር ተቋማት ጋር በጋራ እየተተገበረ በሚገኘው ኢኖቬሽን ልማት ፕሮጀክት በኩል ሀገራዊ የኢኖቬሽን ግንባታ ውስጥ ቁልፍ ሚና ካላቸው የሳይንስና ክፍተኛ ሚኒስቴር እና ከኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ማዕከል ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል፡፡
ይህም ስምምነት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን የትምህርትና ስልጠና እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎች ትስስር የጋራ ምርምር እንዲያካሂዱ፣ውጤታማ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጉ እንዲሁም በጋራ የሚፈጠሩ እና የሚለሙ አዳዲስ ኢኖቫቲቭ ሀሳቦች የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዲያጉ የሚያስችል ሲሆን በኢንተርፕርነርሺፕ ማዕከል በኩል ደግሞ ሀገራዊ ቴክኢንተርፕርነርሺፕን መሰረት ያደረገ የሰው ሀይል ልማትን ማከናወን ነው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በመወከል የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት ክብርት ሚኒስትር ዲ.ኤ.ታ ያኒአ ሰይድመክይ (ፒ ኤች ዲ) እንደተናገሩት ከተለያዩ ተቋሟት ጋር በጋራ በመስራት የኢኖቬሽን ስራዎች በመደገፍና ቴክኖሎጂውን በማዘመን ለማህበረሰባችን ተደራሽ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማሳለጥ አለብን ብለዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱም እንዳሉት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በየአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የምርምርና የፈጠራ ስራዎችን በመስራት እና ቴክኖሎጂዎችን በማሸጋገር የስራ እድል በመፍጠር እና የኢንዱስትሪውን ብሎም የማህበረሰቡን ችግር በመፍታት የምንፈልገውን እድገት ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሀሰን ሁሴንም እንዳሉት የኢኖቬሽን ልማት የመጨረሻ ግቡ የስራ ዕድልን መፍጠር መሆኑን አስታውሰው የዛሬው ስምምነት ይህን ዕውን ለማድረግ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡