የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የበላይ አመራሮች ጋር በመሆን አይሲቲ ፓርክን የጎበኙ ሲሆን ከፓርኩ አመራሮች ጋርም ውይይት አድርገዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በጉብኝቱ ወቅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉን ፖሊሲ፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂና የ10 ዓመቱን ዕቅድ ከመተግበር አንጻር እንዲሁም በመንግስት የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት ለመወጣት እንደ አይሲቲ ፓርክ ዓይነት መሰረተ ልማቶች ወሳኝ ሚና ይኖረዋቸዋል ብለዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም እንደ አይሲቲ ፓርክ አይነት መሰረተ ልማት መንግስት አይሲቲው ዘርፍ ራሱን ችሎ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚኖረውን ተሳትፎ ከመጨመር አንጻርና ሌሎች ወሳኝ የኢኮኖሚው ዘርፎችን ማለትም ግብርናን፣ ቱሪዝምን፣ ትምህርትን፣ ጤናን፣ አምራች ኢንዱስትሪውን እና የአገልግሎት ዘርፉን ምርታማና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የቴከኖሎጂ መፍትሄዎችን ለማበልጸግ አስቻይ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለዋል።

በመሆኑም ፓርኩ በተቀዳሚነት የዘርፉን ጀማሪ ተቋሞች (start ups) ወደ ኩባንያ የሚሸጋገሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለሚፈጠር የስራ ዕድልና የውጭ ምንዛሬ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰጠውን ሃላፊነት ለመውጣት ያስችለዋል ብለዋል።

የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሰንዱካን ደበበም በበኩላቸው በአይሲቲ ፓርኩ ውስጥ እስከአሁን እየተሰሩ ያሉትን ዋና ዋና ስራዎችና ያገጠሙ ተግዳሮቶችን በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የምርምርና ኢኖቬሽን ዘረፍ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፓርኩን በጎበኙበት ወቅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግሉን ዘርፍ መሪነት ከማረጋገጥ አንፃር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀው ለሚመጣውም ለውጥ ሚና ያላቸውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በፓርኩ ውስጥ ስራ ለመጀመር እንቅስቃሴ እያደረጉ ላሉ ኩባንያዎች ገልጠዋል።

በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የአይሲቲ ፓርኩ ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት እንዲሰጥና ትርጉም ባለው መልኩ የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ይቻል ዘንድ ከኢንደስትሪ ፓርኮች ልማትና መሰል መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook