ክቡር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ቀደምት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ካላቸው ሀገራት ውስጥ መሆኗን ጠቅሰው በልማት፣ በባህልና በቅርሶች ጥበቃ እንዲሁም በተመሳሳይ ዘርፎች እየተደረገ ያለው አጋርነትና ትብብር ዕውቅና እንደሚሰጡት አመስግነው ገልፀዋል።
በቀጣይም ከዚህ በፊት በጋራ ሲሰራባቸው የነበሩ የትብብር መስኮችን በማጠናከርና በተጨማሪ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ የተለዩትን ተግባራት ለመፈፀም የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ተባብሮ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት አብራርተዋል።
ክቡር አምባሳደር Remi Marechaux በበኩላቸው ፈረንሳይና ኢትዮጵያ ያላቸውን የቆየ ግንኙነት አውስተውና ሀገራቸው በብዙ መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልፀው በቴክኖሎጂው ዘርፍ በተለይም በስፔስ ሳይንስና በዲጂታላይዜሽን መስኮች ተባብሮ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት እና ዝግጁነት ገልፀዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን መቶ ሃያ አምስተኛ ዓመት ለማክበር በዝግጅት ለይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ክቡር አምባሳደር Remi Marechaux አሁን በኢትዮጵያ ስላለው የሰላም ሁኔታን በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ከፍተኛ ተወካይ እና በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እየተደረገ ያለውን የሰላም ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸው ፈረንሳይ ለዚህ ያላትን ድጋፍ አጠናክራ እነደምትቀጥል አሳውቀዋል።
ክቡር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሰሜን የሃገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትና ቀድሞም በተደጋጋሚ በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ስታደርግበት የቆየችው ጉዳይ እንደነበር ገልፀው የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ከፍተኛ ተወካይ እና በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት በተከበሩት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እየተደረገ ያለውን ጥረት በበጎ ጎኑ እንደሚመለከቱት ገልፀው የመንግስትና ህዝብ ፍላጎት ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን ሀገር የማዳን ጦርነት ባጠረ ጊዜ አጠናቃ ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለስ መሆኑን የፈረንሳይ መንግስት ተረድቶ የኢትዮጵያን ጥረትና አቋም እንዲደግፉ በአፅንኦት ጠይቀዋል።